የፌዴራል መንግስት በጀትና የክልሎች የድጎማ በጀት የክፍፍል ቀመር ህግ ሆኖ ሊወጣ ነው

257

ሰኔ 7/2011 የፌዴራል መንግስት በጀትና የክልሎች የድጎማ በጀት የክፍፍል ቀመር ህግ ሆኖ እንደሚወጣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባካሄደው 5ኛ የፓርላማ ዘመን 4ኛ የስራ ዓመት አፈጻጻም በተመለከተ በዋና ዋና አፈጻጻሞችና ያስተላለፋቸውን ውሳኔዎች አስመልክተው መግለጫ ሰጥቷል።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባሄ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም በዚሁ ወቅት እንዳስታወቁት በ1989 ዓ.ም የወጣው የፌዴራልና የክልሎች የበጀት  ክፍፍል ቀመር ህግ ሆኖ እንዲወጣ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተልኳል።

ቀደም ሲል የበጀት ክፍፍል ቀመር ተብሎ በ1989 ዓ.ም የወጣው አዋጅ የጋራ የገቢ ማካፋፋያ መሆኑን ጠቁመው በእሱ ላይ የፍትሃዊነት ጥያቄዎች ሲነሳ መቆየቱን ተናግረዋል።

አሁን ባለው የአገሪቷ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገትና በፍትሃዊነት ላይም ክፍተት በመኖሩ የቀመር ክፍፍልና የአስተዳደር ስርዓት መሻሻል እንዳለበት ተወስኗል ብለዋል።

የክፍፍል ቀመርና በአስተዳደር ላይ ያለ ችግር በክልሎች መካካል ፍትሃዊ የሆነ ክፍፍል እንዲኖርና በህገመንግስቱ ላይ የተቀመጠ ቢሆንም ፍትሃዊ የእድገት ደረጃ እንዲኖር ለማድረግና የአስተዳደር ስርዓት እንዲሻሻል ለማድርግ ያስችላል ነው ያሉት ወይዘሮ ኬሪያ።

አዋጁ ህግ ሆኖ እንደሚወጣና በ2013 ዓ.ም ተግባራዊ እንደሚሆንም ተናግረዋል።

የፌዴራል ድጎማ በጀት በተመለከትም መመሪያው ህግ ሆኖ እንዲወጣ የፌዴራል መንግስትና በክልሎች የሚከፋፈለው፣የጋራ ገቢዎች የክፍፍል ቀመር ግልጽ እንዲሆንና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እንዲከፋፈል እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።

የፌዴራል መንግስት የመሰረተ ልማት በጀትም ለክልሎች የሚያደረገው ክፍፍል ወጥ የሆነ ስርዓት አልነበረውም ያሉት አፈጉባዔዋ፤ በዚህም ቅሬታዎች ሲነሱ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ከአሁን በኋላ ተቋማዊ ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩንም ጠቁመዋል።

የፌዴራል መንግስት የመሰረተ ልማት ተደራሽነት ለክልሎች ክፍፍል በሚያደርጉ 8 መስሪያ ቤቶች ላይ የፍትሃዊነት ቅሬታ መቅረቡንም ገልጸዋል።

የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የቴሌ፣ የመንገድ፣ የትምህርት ቤት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢንቨስትመንት፣ የመስኖና ኢነርጂ በመስኖ ግድብ ግንባታ እና የኤርፖርቶች አገልግሎት ፍትሃዊ ተደራሽነት ላይ ከክልሎች ቅሬታ መቅረቡን ጠቁመዋል።

የኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥና በህዝቦች መካከል ፍትሃዊ እንዲሆን ማረጋገጫ ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋልም ብለዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልሎች መካከል የተመጣጠነ ዕድገት እንዲኖር ለማስቻልም የፌዴራል መሰረተ ልማት ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ይታወቃል።

የካፒታል በጀትና የፌደራል በጀት ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ክትትል እንዲደረግባቸው ማስፈለጉን ተከትሎም ረቂቅ አዋጁ እንደሚወጣ ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ክልሎች እርስ በርስ እና ከፌደራል መንግሥት ጋር ያላቸው ግንኙነት በህግ ማዕቀፍ ባለመደገፉ ሲያወዛግብ እንደነበረና ይህንን ችግር ለመፍታትም ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መመራቱንም ገልጸዋል።