ክልሉ የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጹ

72
ጎባ ሰኔ 7  2011 የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስታወቁ። በባሌ ሮቤ ዛሬ ከባሌ ዞን 18 ወረዳዎችና ሦስት ከተሞች አስተዳደር የሕዝብ ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል። ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ሽመልስ አብዲሳ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት የክልሉ መንግሥት በክልሉ ተንሰራፍተው የቆዩትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማስወገድ ይሰራል። ክልሉ በአገሪቱ በፖለቲካው መስክ የተገኘውን ድል መንከባከብና ኢኮኖሚውን መደገፍ እንደሚገባ ያመለከቱት አቶ ሽመልስ፣ የልማት እንቅስቃሴውን በሕዝቡ የልማት ተሳትፎ ይጠናከራል ብለዋል። በዞኑ የተጓተቱ የልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነት ተጠናቀው ለሕዝብ አገልግሎት እንደሚውሉም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥት በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ የሚሰሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በነፃነት እንቅስቃሴያቸውን እንዲቀጥሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ሁሉ፤ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ በሚያደርጉት ላይ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን እንደሚሰራም አስታውቀዋል። በዞኑ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለማቋቋም የሚፈልጉ አርሶ አደሮች በኅብረት ሥራ ማህበራት በመደራጀትና ከባንኮች ብድር ወስደው መሥራት እንደሚችሉም አስረድተዋል። የሕዝብ ተወካዮቹ  ዞኑ ምርት ትርፍ አምራች ቢሆንም፤ በመንገድ እጥረት ምርቱን ለገበያ ለማውጣት ችግር እንደገጠመ ገልጸዋል። የሮቤ ከተማ አስተዳደር መሬት ማስተር ፕላን ስለሌላት ሕገ ወጥ የመሬት ወረራና በከተማዋ አካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮች መፈናቀል መፍትሄ እንዲፈልግ የጠየቁም ተወካዮች ነበሩ። የአካባቢውን ግብዓቶች የሚጠቀሙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መቋቋም፣የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያመጡና ሥራ የሚፈጥሩ የግብርና ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ትኩረት እንዲሰጣቸው የሚያሳስቡ አስተያየቶች በመድረኩ ቀርበዋል። ተሳታፊዎቹ በምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ለሚመራው የክልል መንግሥት ልዑካን ቡድን የባህል አልባሳት ሽልማት ተበርክቶለታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም