መገናኛ ብዙሃን ትክክለኛና ፈጣን መረጃ ለህዝቡ ማድረስ ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባ ተገለጸ

180

ሰኔ 7/2011 መገናኛ ብዙሃን ትክክለኛና ተአማኒነት ያለውን ፈጣን መረጃ ለህብረተሰቡ ማድረስ ቀዳሚ አጀንዳቸው ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ።

“በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ የመረጃ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ መገናኛ ብዙሃንና የኮሙዩኒኬሽን ሚና” በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ዩኔስኮ ድርጅት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ስልጠና በአዳማ ከተማ እየተካሔደ ነው።

በመድረኩ ላይም ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት  ቤት ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ንጉሴ መሸሻ እንደተናገሩት መገናኛ ብዙሃን የተከታዮቻቸውን ፍላጎት በማጤን ፈጣን፣ ወቅታዊና ተዓማኒነት ያለውን መረጃ በማድረስ ላይ ሊያተኩሩ ይገባል።

በአሁኑ ወቅት የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን የይዘት ስራ ደካማ መሆንና የፕሮግራሞቻቸውም ለገንዘብ ምንጮቻቸው /ስፖንሰሮቻቸው/ ጥገኛ መሆን ከፈጻሚው አቅም ማነስ ጋር ተደማምሮ የዘርፉ ፈተና መሆኑን ተናግረዋል።

በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገጾች የሚተላለፉ የተሳሳቱ መረጃዎችን ለማጥራት ከመሞከር ይልቅ የራሳቸውን ፈጣንና በቂ መረጃ ለህብረተሰቡ ማድረስ እንደሚገባም አስረድተዋል።

ያሉባቸውን የመረጃ እጥረቶች ተሻግረው ከርዕዮት አለም፣ከፖለቲካ አመለካከትና ፕሮፓጋንዳ ገለልተኛ በመሆን ህዝቡን ወደ ትክክለኛ ጎዳና መምራት ከዘርፉ የሚጠበቅ ሃላፊነት መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ በቀለ ሙለታ በበኩላቸው በአገሪቷ የተፈጠረውን የለውጥ አጋጣሚ በመጠቀም ለማህበረሰቡ ትክክለኛና ታማኝ መረጃ ማድረስ ከመገናኛ ብዙሃንና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፉ የሚጠበቅ ነው ብለዋል።

መገናኛ ብዙሃን እያጋጠሟቸው ከሚገኙት ተግዳሮቶች አንዱና ዋነኛውም የመረጃ ንፍገት መሆኑን ጠቁመው  የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ክፍተቱን ለመሙላት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ዜጎች መረጃን መረዳት በሚችሉበት መልኩ ማሰባሰብ መተንተንና ማሰራጨት የመገናኛ ብዙሃኑ ተግባር እንደመሆኑም ትክክለኛ መረጃን በወቅቱ ለህዝቡ ተደራሽ በማድረግ ረገድ ተቋሙ የድርሻውን ለመወጣት  እንደሚሰራም ገልጸዋል።

ስልጠናው በአሁኑ ወቅት ከማህበራዊ ሚዲያ መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሚኖረውን የመረጃ መዛባት፣  ውዠንብሮችና ማደናገር ለማረም ጭምር የጋራ አቅጣጫ የሚያስይዝ መሆኑንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እራሱን በአዲስ መልክ ያደራጀበትን አላማ ለማሳካትም የመገናኛ ብዙሃኑን ክፍተቶች በተለይም የመረጃ ምንጭ እጥረት እና ሚዛናዊነት ችግሮችን ለማቃለል እንደሚሰራ አመልክተዋል።

በአዳማ ከተማ ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ  ላይ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች እና አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።