የመቀንጨር ችግርን ለመከላከል የምግብና የስርአተ ምግብ ተግባቦትን ማስረጽ ይገባል

101
ሰኔ7/2011 በሀገሪቱ የመቀንጨር ችግርን ለመከላከል የምግብና የስርአተ ምግብ ተግባቦትን በህብረተሰቡ ውስጥ በአግባቡ ማስረጽ እንደሚገባ ተገለጸ። በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተዘጋጀው የሰቆጣ ቃል ኪዳን የተግባቦትና ህዝብ ግንኙነት ሥራዎች ማበልፀጊያና ማሳለጫ የውይይት መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ እንዳሉት የመቀንጨር ችግርን የመዋጋት ሥራ ዘርፈ ብዙና የሁሉንም አካል ተሳትፎና ጥረት የሚጠይቅ ነው። በተለይም በግንዛቤ ማነስ ስር የሰደደ የስርአተ ምግብ ጉድለት መኖሩ በመላ ሀገሪቱ የመቀንጨር ችግር በስፋት እንዲከሰት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። የመቀንጨር ችግርን ለመፍታት የምግብና የስርአተ ምግብ ተግባቦትን ህብረተሰቡ ውስጥ በአግባቡ ማስረጽ ወሳኝ መሆኑን ዶክተር ጌታቸው አስታውቀዋል። እንደእርሳቸው ገለጻ የሚዲያና የኮሚኒኬሽን አካላት የሕይወት ዘመን አስተማሪዎች በመሆናቸው ሙያቸው የሚፈጥረውን ዕድል ተጠቅመው የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ አለባቸው። “ቀጣይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በመስራት በስርአተ ምግብ ላይ የተሻለ እውቀት ያለው ማህብረሰብ ማፍራት ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል። በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእናቶችና ህጻናት ጤና ዳይሬክተር ዶክተር መሠረት ዘላለም በበኩላቸው በሀገሪቱ የመቀንጨርና መቀጨጭ ችግሮች አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ለመቀንጨር ችግር ከሚያጋልጡ ሁኔታዎች መካከል የምግብ ዋስትና ችግር፣ የአካባቢና የግል ንጽህናን አለመጠበቅ ፣ የእናቶችና ህፃናት ጤና እንክብካቤን በወቅቱ አለመጠቀምና የጥራት መጓደልን ለአብነት አንስተዋል። “ በአብዛኛው ጠንካራ የተግባቦት ስራ በመስራት የመቀንጨር ችግርን መፍታት ይቻላል” ያሉት ዳይሬክተሯ፣ የኮሚኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በየተቋማቸው የመቀንጨር ችግር እንዲቀንስ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ጠይቀዋል። ባለፉት 10 ዓመታት መንግስት፣ አጋር አካላትና ማህብረሰቡ ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ የህጻናት የመቀንጨር ችግርን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጣር በ2000 ዓ.ም ከነበረበት 58 በመቶ ወደ 38 ነጥብ 4 በመቶ መቀነስ መቻሉን ዶክተር መሰረት አስታውቀዋል። በሚኒስቴር መስሪያቤቱ የሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮግራም ከፍተኛ ማናጀር ዶክተር ሲሳይ ሲናሞ በበኩላቸው በሀገሪቱ የመቀንጨር ችግርን እስከ 2022 ዓ.ም ዜሮ ለማድረስ መንግስት የ15 ዓመት ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ለተግባራዊነቱ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። በዚህ እንቅስቃሴም ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ 7 ሚሊዮን 852 ሺህ ህጻናትን ከመቀንጨር ችግር ለመከላከል መታቀዱን ተናግረዋል። ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው በዚህ መድረክ ላይ በፌዴራልና በክልል የሰቆጣ ቃል ኪዳን ፈጻሚ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነቶች ኃላፊዎችና ባለሙያዎች መሳተፋቸው ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም