አተትን ለማከም…ግንዛቤ ይቅደም!

265

በሃብታሙ አክሊሉ (ኢዜአ)

ገና ከጅምሩ የበሽታው ትክክለኛ መንስኤ የአየር መበከል እንደሆነ ይታመን ነበር። እኤአ በ1840ዎቹ መጨረሻ ጆን ስኖው የተባለ እንግሊዛዊ ሃኪም የኮሌራ መሽታ ከተበከለ አየር ሳይሆን ከተበከለ ውሃ ሊከሰት እንደሚችል ሀሳብ አቀረበ። የሃሳቡን ትክክለኛነት ለማረጋገጥም በለንደን ከተማ ሶሆ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነዋሪ በሆኑ የኮሌራ በሽታ ተጠቂ ሰዎች ላይ ባደረገው ጥናት ከአንድ መስመር የሚመጣ የተበከለ ውሃን ለመጠጥነት እንደሚጠቀሙ አረጋገጠ።

በጊዜው የስኖው ግኝት አስደንጋጭ ሁኔታን ፈጥሮ እንደነበርና እኤአ በ1854 ፊሊፖ ፓቺኒ የተባለ ጣሊያናዊ ሳይንቲስት ኮሌራ አምጪ ረቂቅ ተሃዋሲያን ላይ ባካሄደው ምርምር ተስፋ ሰጪ ግኝትን በማምጣቱ በሽታውን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ላይ አዲስ ምዕራፍን ከፈተ። ከዚያም በኋላ የበለፀጉ ሃገራት በበሽታው እምብዛም ፈተና ውስጥ ሲወድቁ አይታይም። ችግሩ አሁንም የታዳጊ ሃገራት እንደሆነ ዘልቋል።

የኮሌራ በሽታ በይበልጥ የደሃ ሃገራት ህዝቦችን በየጊዜው እየደጋገመ ያጠቃል። የበሽታው ስርጭት እኤአ ከ2005 ጀምሮ በተጠቀሱት ሃገራት እየጨመረ እንደመጣ የአለም አቀፉ የጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል። የኮሌራ(የአተት) በሽታ ኢትዮጵያን በመሰሉ የመሰረተ ልማት ዕድገታቸው ውስን በሆኑ ሃገራት ህዝቦች ላይ ተዛምቶ በርካቶችን ለሞት ሲዳርግ ይስተዋላል።

የአካባቢና የግል ንፅህናን በወጉ በማይጠበቅባቸውና ሰዎች ተፋፍገው በሚኖሩባቸው አካበባዎች ላይ የበሽታው ክስተት ወደ ወረርሽኝ የሚለወጥበት አጋጣሚም ተደጋግሞ የታየ ጉዳይ ነው። በተለይ በሃገራችን አሁን የክረምት ወቅት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ጎርፍ በየቦታው ስለምከሰት የበሽታው ስርጭት ሰፊ ቦታዎችን ሲያዳርስ ይታያል።

የኮሌራ በሽታ ቫይብሮ ኮሌራ በተባለ ተሃዋሲ አመካይነት የሚመጣ፣ በተበከለ ምግብና ውሃ ምክንያት የሚከሰት በሽታ ነው። በሽታው አንጀትን በማጥቃት አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከትን የሚያስከትል ምልክት አለው። አንድ በበሽታው የተያዘ ሰው በበሽታው በተያዘበት ፍጥነት ተገቢውን ህክምና ካላገኘ በሰውነቱ ያለው ፈሳሽ ተሟጦ ያልቅና አቅምን በማሳጣት ለሞት ይዳረጋል። በሽታውን አስመልክተው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በሽታው በአብዛኛው በሰዎች ላይ ምልክቱ የሚታየው በባክቴሪያው ከተለከፉ ከሁለት ወይም ከሶስት ቀናት በኋላ ነው።

በሽታው በሃገራችንም ጊዜውን ጠብቆ የመከሰቱን ጉዳይ ከሰሞኑ በመገናኛ ብዙሃን ከሚተላለፉ መረጃዎች ለመገንዘብ ችለናል። እንደ መረጃዎቹም በሽታው መዲናችን አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች ክልሎች ተከስቶ ለሞት ያበቃቸው ሰዎች እንዳሉና በርካቶች በበሽታው መያዛቸው ይነገራል።

በቀላሉ ንፅህናን በመጠበቅ ለመከላከል የሚቻል በሽታ ስለምን በያመቱ እየመጣ እንዲጎበኘን ሆነ?…ለወትሮው ከክረምት ወቅት ጋር ተያይዞ የሚመጣ በሽታ መሆኑ እየታወቀ ለምን ቅድመ ጥንቃቄ ሊጎድለን ቻለ?…የሆነስ ሆነና በሽታው ከተጠቀሰው በዘለለ በወረርሽኝ መልክ እንዳይከሰት ምን እየተደረገ ይሆን?…የሚሉት ጥያቄዎች መቼም በአዕምሮአችን ደጋግመው ሊመጡ እንደሚችሉ ይታሰባል።

ከሰሞኑ ከበሽታው ክስተት እኩል የበሽታው ስያሜ ጉዳይ ትኩረትን ስቦ ነበር። ለመሆኑ አሁን የተከሰተው ኮሌራ ነው ወይስ አተት የሚለው ጉዳይ ቅድሚያ ምላሽ ሊያገኝ ይገባል የሚሉ ወገኖች ተበራክተው ሰንብተዋል። ምክንያቱም ከዚህ ቀደም ለአመታት አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት(አተት) ሲባል ስለከረመ መጠየቁ አይከፋምና ነው። ‘በሽታውን የደበቀ …‘ የሚባለው ነገር እንዳይደርስብንም የበሽታውን ምንነት ማወቁ ተገቢ ይመስለናል።

የጤና ሚኒስቴር እና የህብረተሰብ ጤና ኢንቲትዩት ሰሞኑን ከበሽታው ክስተት ጋር ተያይዞ ባወጡት መረጃም በአተት ከተያዙት ሰዎች ውስጥ በኮሌራ የተጠቁ ሰዎች መኖራቸውን ለማወቅ ተችሏል። የጤና ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚር አማን በቅርቡ ከዶቼቬሌ ጋር በነበራቸው ቆይታ በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ ክልሎች እና በአዲስ አበባ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች በአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት መያዛቸውን ተናግረው ከተጠቀሰው ቁጥር ዘጠኝ የሚሆኑት በቫይብሮ ተሃዋሲ በመለከፋቸው የኮሌራ በሽታ እንደተገኘባቸው ተናግረዋል። እንደ ሚኒስትሩም ኮሌራ ሁሉ አተት ሊሆን እንደሚችልና አተት ሁሉ ግን ኮሌራ ሊሆን እንደማይችል ነው።

በአዲስ አበባ በሚገኙ በሁሉም ክ/ከተሞች ሊባል በሚችል መልኩ በሽታው እንደተከሰተ ከግምት በማስገባት ህብረተሰቡ የግሉን እና የአካበባውን ንፅህና መጠበቅ ችላ ሊለው አይገባም። ለምግብ እና ውሃ ጥቅም ላይ የሚውሉ የመገልገያ ዕቃዎች በንፅህና ከመያዝ ባሻገር ውሃን አፍልቶ ወይም ደግሞ አክሞ ለመጠጥነት መጠቀም እንደሚገባ የህክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ።

መጸዳጃ ቤት ደርሰው ሲመለሱም ሆነ ከመመገብ አስቀድሞ እጅን ቢቻል በሳሙና ካልሆነም በውኃ በደንብ መታጠብ፤ ምግብን በደንብ አብስሎ መመገብ እና የመመገቢያ ቁሳቁሶችን በንፅህና በመያዝ መጠቀም ይመከራል። የበሽታው ምልክት የታየበት ሰዉ በቂ ፈሳሽ መውሰድና በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም መሄድ እንደሚኖርበትም ባለሙያዎቹ ይመክራሉ።

በሽታው ተባብሶ አስከፊ ጉዳትን እንዳያደርስ መንግስት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ የተናገሩት ዶ/ር አሚር ህመምተኞች ፈጣን የሆነ የህክምና እገዛን እንዲያገኙ የሚያስችል ስራ ከየክልል መስተዳድሮች ጋር  በመተባበር እየተሰራ እንደሆነም አንስተዋል። ሰዎች በብዛት በሚሰበሰቡባቸው እንደ ቤተክርስቲያን እና መስጊዶች አካባቢ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው።

በበርካታ የፀበል አካባቢዎች ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግ የሚያሳስብ መልዕክትንም ቤተ ክህነት ማስተላለፏም ተገልጿል። ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመተባበር  ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በአንድ ቦታ ላይ ለሚገኙ ዜጎችም የጤና እገዛ ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስቴር በሽታው ከመከሰቱ አስቀድሞ ከአለም የጤና ድርጅት ጋር በመተባበር የዳሰሳ ጥናት ማድረጉን ዶ/ር አሚር ተናግረው ጥናቱን መሰረት በማድረግም 730 ሺ ክትባት ከለጋሾች እንደተገኘ ጠቁመዋል። ለወደፊት የበሽታው ተጋላጭ በሆኑ አከባቢዎች በቋሚነት ክትባት ለመስጠት እንደታሰበም ለማወቅ ተችሏል። በአለም ላይ የኮሌራ በሽታን ለመከላከል የሚዘጋጀው የክትባት አቅርቦት አነስተኛ መሆኑ ጉዳዩን አስቸጋሪ ሊያደርገው እንደሚችልም ተነስቷል።

የህብረተሰብ የጤና ትምህርቶችን በማስፋፋት፣ በቀላሉ ንፅህናን በመጠበቅና ሌሎች ጥንቃቄዎች በማድረግ፣ ለመከላከል ጥረት በማድረግ ኮሌራንም ሆነ አተትን መከላከል እንደሚቻል ባለሙያዎች ዘወትር ይመክራሉ። የኮሌራ በሽታ ክትባት ዋጋው ውድ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የበሽታው ተደጋግሞ መከሰት እንደ እኛ ላለ ሃገር ምን ያህል ዋጋ ሊያስከፍለን እንደሚችል መገመቱ ቀላል ነው።

ስለሆነም ህብረተሰቡ የቆሻሻ አወጋገዱን ስርአት በማስያዝ የግልና የአካባቢውን ንፅህና እንዲጠብቅ ማስተማር ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ ነው። መንግስትም የመሰረተ ልማት አውታሮችን በየጊዜው በሚያወጣቸው ዕቅዶች ውስጥ በማካተት ተፈፃሚ እንዲሆኑ ጠንካራ ክትትል እና ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል።