ብሔራዊነትና ብሔርተኝነት ተጣጥመው ይሄዳሉ ወይስ አብረው አይቆሙም?

510

ሰኔ 7/2011 በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት “አዲስ ወግ” በሚል ርዕስ ዛሬ ባተካሄደው ምሁራዊ ውይይት በብሔርተኝነት ጉዳይ ላይ ሰፊ ምክክር ተደርጓል።

የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የተለያዩ ሃሳቦች ከአደባባይ ወደ መድረክ የማምጣትን ግብ አስቀምጦ አዲስ ወግ በሚል ርዕስ የተለያዩ የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀት ከጀመረ ወራቶች ተቆጥረዋል።

የህግ የበላይነት፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሉ ጉዳዮች ከዚህ በፊት በተደረጉ መርሃ-ግብሮች ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን፤ ዛሬ ደግሞ ብሔርተኝነት በኢትዮጵያ በሚል ርዕስ ምሁራዊ ምክክር ተደርጓል።

በመድረኩ የጤና ባለሙያው ዶክተር ዳዊት ወንድማገኝ እንዲሁም የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን የሆኑት ዶክተር አብዲ ዘነበ እና ሙሳ አደም የመወያያ መነሻ ሃሳብ አቅርበዋል።

ዶክተር ዳዊት በዚህ ወቅት የማንነት ጉዳይ በብሔር ብቻ ሳይሆን በጾታ፣ ሃይማኖትና ሌሎች ጉዳዮች እንደሚገለጽ ጠቁመው፤ ከዚህ አንጻር “የተለየ ማንነት እንጂ የተሻለ ማንነት የለም” ብለዋል።

ሰው በማንነቱ የማይጨቆንበት እንጂ ማንነት የሌለበት ዓለምን መፍጠር እንደማይቻልም ገልጸዋል።

በመሆኑምበጥቅሉ ማንነትም ሆነ ከማንነት አንዱ መገለጫ የሆነው ‘ብሔር’ የግጭት ምክንያት ሊሆን አይችልም ነው ያሉት።

ዶክተር አብዲ ዘነበ በበኩላቸው የብሔራዊነትና የብሔርተኝነት እንቅስቃሴዎች በጥቅል ሲታዩ ከፋፋዮች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ‘ብሄርተኝነትንና ብሄራዊነትን እናሰፍናለን’ በሚሉ ቡድኖች የበርካታ ዜጎችን ህይወት የቀጠፉ  እንቅስቃሴዎች መካሄዳቸውን ላነሱት ሃሳብ በአስረጂነት አቅርበዋል።

ነገር ግን ሁለቱም ቡድኖች ውጥናቸውን ሙሉ ለሙሉ ማሳካት አለቻሉም ያሉት ዶክተር አብዲ፤ አሁን ላይ የሚበጀው  ሁለቱም የኢትዮጵያ ፖለቲካ አካል መሆናቸውን አምኖና አጣጥሞ መሄድ መሆኑን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያዊያን ምንም ጥቅም በሌላቸውና በተሳሳቱ መረጃዎች ዘመናትን የተሻገረ ግጭት ውስጥ እንደነበሩ ያስታወሱት ደግሞ አቶ ሙሳ አደም ናቸው።

በታሪክ አጋጣሚ የተሰሩ ስህተቶችን በማረም፣ አንድ የሚያደርጉ ጉዳዮችን በማጠንከርና ልዩነቶችን በማክበር የተሻለ አገር መገንባት እንደሚቻልም አውስተዋል።