የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀድሞ ቀያቸው መመለስ የሚያስችል አንጻራዊ ሰላም ተፈጥሯል - የሰላም ሚኒስቴር

69
ሰኔ 7/2011 በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደቀድሞ ቀያቸው መመለስ የሚያስችል አንጻራዊ ሰላም የተፈጠረ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ። ባለፉት ስድስት ወራት 1 ነጥብ 8 ሚሊዬን ዜጎች ወደቀያቸው ተመልሰዋል። የሰላም ሚኒስቴር የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማስመለስ የተከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ ከፌደራልና ክልል ባለድርሻ አካላት ጋር በአዲስ አበባ ውይይት አድርጓል። "በኢትዮጵያ እስከ ሶስት ሚሊዬን ዜጎች ተፈናቅለዋል የሚሉ አካላት ቢኖሩም መንግስት የሚያወቀውና ትክክለኛው መረጃ 2 ነጥብ 3 ሚሊዬን" ነው ሲሉ የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል በውይይቱ ላይ ተናግረዋል። የፈደራልና የክልል መንግስታት ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ካለፈው ታህሳስ ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ ባከናወኑት ተግባርም 1 ነጥብ 8 ሚሊዬን ዜጎችን ወደቀያቸው መመለስ መቻሉን አክለዋል። ወይዘሮ ሙፈሪያት እንዳሉት፤ መንግስት ቀሪዎቹን ዜጎች እስከ ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም  ሙሉ በሙሉ ወደቀድሞ መኖሪያቸው ለመመለስ እየሰራ ነው። በመሆኑም ባለፉት ወራት ከተመለሱት አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዬን ዜጎች በተጨማሪ ቀሪዎቹን 500 ሺህ ተፈናቃዮች በቀሪዎቹ ቀናት ለመመለስ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህ ደግሞ በሁሉም ክልሎች ከቀበሌ እስከ ዞን በየደረጃው ያሉ አመራሮችና የኅብረተሰብ ክፍሎት ስራውን በባለቤትነት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። ተፈናቃዮች ካሁን በፊት ወደቀያቸው የተመለሱት በፍላጎታቸው መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ በቀጣይም ግንዛቤ መፍጠር እንጂ በማስገደድ እንዲመለሱ አይደረግም ነው ያሉት። የህግ የበላይነትን በማስከበር ተፈናቃዮች ያሉበትን አካባቢ ከስጋት ነፃ ማድረግ እንቅስቃሴ እየተሻሻለ መምጣቱንም ወይዘሮ ሙፈሪሃት አብራርተዋል። "በቀጣይም ተመሳሳይ የመፈናቀል ችግር እንዳይከሰት ከሚመለከታቸው የፌደራልና የክልል መንግስታት፣ ከኅብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንሰራለን" ብለዋል። የብሄራዊ አደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በበኩላቸው፤ ህግ የማስከበር ሂደቱ በቂ ባይሆንም ወንጀለኞች ለፍርድ እየቀረቡ መሆኑን ገልፀዋል። በዚህም በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝና የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች 1ሺህ 320 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን አመልክተዋል። "በተደራጀና በታቀደ መልኩ ግጭት የሚቀሰቅሱ ወንጀለኞችን ለፍትህ አደባባይ ማቅረብ ለነገ ይደር የማይባል ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም