አዲስ አበባ በዘላቂ ልማት ግቦች ላይ ያተኮረ የቢዝነስ ጉባኤ በቀጣዩ ሳምንት ታስተናግዳለች

60
ሰኔ 5/2011 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት "ዘላቂ የልማት ግቦች" በሚል በቀረፀውና መላው የዓለም አገራት እየተገበሩት ባለው የልማት ውጥን ላይ ያተኮረ የቢዝነስ ጉባኤ በቀጣዩ ሳምንት በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የአዲስ አበባ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አስታወቀ። ከመጪው ሰኔ 13 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚካሄደውን ጉባኤ በመተባበር ያዘጋጁት የአዲስ አበባ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትና በዴንማርክ የሚገኘው የዴኒሽ ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን ናቸው። የቢዝነስ ጉባኤው የሚካሄደው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል። በጉባኤው ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን፣ የዓለም አቀፍ ድርጅት መሪዎች ተወካዮችንና የፖሊሲ አውጪዎችን ጨምሮ ከ200 በላይ የኢትዮጵያና የሌሎች አገራት ኩባንያዎችና ባለድርሻ አካላት ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ምክር ቤቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ ጠቁሟል። በጉባኤው የኢትዮጵያ የፖሊሲ ቅኝት በዘላቂ የልማት ግቦች አኳያ የተለያዩ አገራት የዘዓቂ ልማት ግቦችን ለማስፈጸም የኢትዮጵያ እና የውጭ ግሉ ዘርፍ ተሳትፎን የሚቃኙ ተሞክሮዎች ይቀርቡበታል ነው የተባለው። እ.አ.አ እስከ 2030 ድረስ ለሚዘልቀው የዘላቂ ልማት ግቦች ስኬታማነት የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ለመቋቋም መንግስታት እና የግሉ ዘርፍ ያላቸው ሚና ላይም ውይይት እንደሚደረግ በመግለጫው ተጠቅሷል። በጉባኤው ላይ የተለያዩ የፓናል ውይይቶች እንደሚካሄዱና የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት በሚያስችሉ የፋይናንስ አማራጮች ዙሪያ ያሉ ተግዳሮቶችና መፍትሄዎች ተለይተው እንደሚቀርቡም ተገልጿል። አፍሪካ ከያዘችው ከ2063 አጀንዳ ጋር የዘላቂ ልማት ግቦች ያላቸው መስተጋብር በተመለከተ ምክክር ይደረጋል። ጉባኤው የዘላቂ ልማት ግቦችን ለመተግበር የግሉን ዘርፍ የሲቪክ ማህበራትንና መንግስትን ያካተተ የጋራ የቅንጅት መድረክ ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል። የዘላቂ ልማት ግቦች እ.አ.አ 2015 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 70ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት የድርጅቱ አባላት እ.አ.አ እስከ 2030 የሚተገበር የዘላቂ ልማት ግቦች የውሳኔ ሀሳብ ማጽደቃቸው የሚታወስ ነው። ለ15 ዓመት የሚተገበሩት ግቦች 17 አላማዎችን የያዙ ሲሆን ድህነትን ማስወገድ፣ጥራት ያለው ትምህርት፣የጾታ እኩልነት፣ንጹህ ውሃና መጠለያ፣ጤና አጠባበቅ፣ተመጣጣኝና ንጹህ የሃይል አቅርቦት ማግኘት እና ሰላምን ማረጋገጥ ዋንኞቹ ግቦች ናቸው። ኢትዮጵያም በዋንኛነት ድህነትን በማስወገድ፣በጤና አጠባበቅ እና የጾታ እኩልነትን በተመለከተ የተቀመጡትን የዘላቂ ልማት ግቦች ውጤታማ በሆነ መልኩ እየተገበረች መሆኑን የተለያዩ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም