ሴቶች የፈጠራ ስራ ላይ ቢሰማሩ ውጤታማ መሆን ይችላሉ- ሴት ተማሪዎች

266

ሰኔ 5/2011 በኢትዮጵያ ሴቶች የፈጠራ ስራ ላይ ቢሰማሩ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ በፈጠራ ስራ ተወዳድረው ተሸላሚ የሆኑ ሴት ተማሪዎች ተናገሩ።

ዘጠነኛው ሀገር አቀፍ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሽልማት ጠቅላይ ሚኒሰትር ዶክተር አብይ ፣ የኢኖሼሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ሌሎች ከፍተኛ ሀላፊዎች በተገኙበት ዛሬ ተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ከአጠቃላይ ትምህርት ተማሪዎችና መምህራን፣ የቴክኒክና ሙያ ሰልጣኞችና አሰልጣኞች፣ የምርምርና የፈጠራ ባለሙያዎች በአጠቃላይ 194 ግለሰቦች የተሸለሙ ሲሆን 24ቱ ሴቶች ናቸው።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የገለጹ ሴት ተሸላሚዎች እንደተናገሩት በፈጠራ ስራዎች ላይ ተግዳሮቶች የሚያጋጥሙ ቢሆንም ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ መፍትሄ እንደሚገኝ በማመን ጠንክሮ መስራት ይገባል፤ በዚህም ነው  ለውጤት መብቃት የሚቻለው።

የጅማ ዩንቨርስቲ ተማሪ የሆነችው ሊዲያ ውብሸት ከሌሎች አራት ሴት ተማሪዎች ጋር በመሆን እናቶች  በምጥ ወቅት የሚገጥማቸውን ችግር በህክምና ለመደገፍ የሚያስችል የህክምና መሳሪያ መስራታቸውን ትናገራለች።

የፈጠራ ስራውን በሚሰሩበት ወቅት ያጋጠማቸውን ችግሮች በመቋቋም ለውጤት መብቃታቸውንም ገልጻለች።

“ሴቶች ለመስራት ያቀዱትን ነገር ከማከናወን የሚያግዳቸው ነገር አለመኖሩን በማመንና በመትጋት ሊሰሩ  ይገባል” ትላለች።

የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ትንሳኤ እናውጋው ዕጽዋትን በመጠቀም የሰው ቆዳ አካል በጸሀይ ብርሃን እንዳይጎዳ የሚከላከል ቅባትና የዝገት ማጥፊያ ኬሚካል ሰርታ ለሽልማት በቅታለች።

እርሷ እንደምትለው ሴቶች ከወንዶች በተሻለ መስራትና ነገሮችን ከተለያዩ አቅጣጫ የማየት ችሎታ ስላላቸው በፈጠራ ስራ ቢሰማሩ ስኬታማ መሆን እንደሚችሉ ተናግራለች።

የ9ኛ ክፍል ተማሪዋ ዘይባ መሃመድ ደግሞ ቅጠላ ቅጠል በመቀመም ሳሙና የሰራች ሲሆን የፈጠራ ስራ ለመስራት ችግሮች ቢያጋጥሙም በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ የተሻለ ነገር ማግኘት የሚቻል በመሆኑ ሴቶች ወደ  ፈጠራ ስራ እንዲገቡ መክራለች።

የኢኖሼሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር የፈጠራ ስራ ማበልጸጊያ ማዕከላትን በማበልጸግ ነባር አሰራሮችን የመቀየር፣ የፈጠራ ስራዎች ወደ ገበያ እንዲቀርቡና ፋይናስን ጨምሮ የተለያዩ ስልጠናዎችን ያካተተ ድጋፍ ለማድረግ  መዘጋጀቱን አስታውቋል።

የፈጠራ ባለቤቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የህግ ማዕቀፍም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እየተዘጋጀ መሆኑም  ተገልጿል።