ለኮሌራ በሽታ አጋላጭ የሆኑ አከባቢዎችን በመለየት የቅድመ ጥንቃቄ ስራ እየተከናወነ ነው

84
ሰኔ 5/2011 በከተማዋ ለኮሌራ በሽታ አጋላጭ የሆኑ አከባቢዎችን በመለየት የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች እየተከናወነ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ምግብ፣መድሃኒት እና ጤና እንክብካቤ አስተዳደር እና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ፡፡ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ወረቲ እንዳሉት በሀገሪቱ አንድ አንድ ክልሎች የተከሰተውን የኮሌራ በሽታ በአዲስ አበባ እንዳይከሰት አስቀድሞ የመከላከል ስራዎች እየተከናወነ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ለበሽታው አጋላጭ የሆኑ የከተማዋ ሁኔታ መለየታቸውን የገለጹት ሃላፊው ከእነዚህም አንዱ የምግብ ተቋማት ይገኙበታል ብለዋል፡፡ በተለይም በከተማዋ ወንዝ ዳር የሚመረቱ አትክልቶች እና ህገ ወጥ እርድ ለኮሌራ በሽታ አጋላጭ ከሆኑ ምክንያቶች በቅድሚያ የሚጠቀሱ በመሆናቸው ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግባችዋል ነው ያሉት፡፡ የምግብ እና ምግብ ነክ አቅራቢ ድርጅቶች ንጽህና አጠባበቅ ላይ ቁጥጥር እየተደረገ እንደሆነ የተናገሩት     አቶ ጌታቸው፤ በእነዚህ ተቋማት የሚሰሩ ሰራተኞችም  የጤና ምርመራ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡ በጎዳና ላይ ምግብ በመሸጥ የሚተዳደሩ ሰዎች በቂ የውሃ አቅርቦት ሊኖራቸው ይገባል ያሉት አቶ ጌታቸው፤ ህብረተሰቡ በጎዳና ላይ የሚሸጡ ምግቦችን በጥንቃቄ መመገብ እንደሚገብም አሳስበዋል፡፡ ክረምቱን ተከትሎ በከተማዋ ኮሌራ እንዳይከሰት ነዋሪው ጥንቃቄ እንዲያደርግም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከል እና መቆጣጠር ባለሙያ  አቶ ቢንያም ተጫኔ በበኩላቸው፤ የኮሌራ በሽታ  እንዳይከሰት  በከተማ ደረጃ ግብር ሃይል ተቋቁሞ የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጿል። በሽታውን ለመቆጣጠርር የሚያስችል የሰው ኃይል ማዘጋጀት እንዲሁም ህብረተሰቡ በበሽታው ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው የማድረግ ስራ እየተሰራ እንደሆነም ጠቅሰዋል። በተለይ በከተማዋ  በቂ መሰረተ ልማት ያልተማላላቸው አንድ አንድ አከባቢዎች ለኮሌራ በሽታ ይበልጥ ተጋላጭ በመሆናቸው በትኩረት እየተሰራባቸው መሆኑን የጠቀሱት ባለሙያው፤ በሽታውን ለመከላከል ህብረተሰቡ የግሉንና የአካባቢውን  ንጽህና እንዲጠብቅም አሳስበዋል፡፡ በሽታው “በምንመገበው ምግብ እና ከምንጠጣው መጠጥ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ነው” ያሉት ባለሙያው፤ ህብረተሰቡ ምግቦች ንጽህናቸውን የጠበቁ መሆናቸው ማረጋገጥ እና  አብስሎ  መመገብ እንዳለበትም መክረዋል። ለተለያዩ  አገልግሎት የሚውል  ውሃ የፈላ ወይም የታከመ መሆን እንዳለበት መልዕክት ያስተላለፉት         አቶ ቢያም፤ ከምግብ በፊትና ከመፀዳጃ ቤት መልስ በሳሙና እጅን መታጠብም በኮሌራ በሽታ ላለመያዝ ሌላኛው የመከላከያ መንገድ  ነው ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም