የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሱዳን ጉብኝት አንድምታዎች በአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን

110

በኢዜአ ሞኒተሪንግ

ያለፈው ሳምንት መገባደጃ በርካታ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያን አስመልክተው ሰፋ ያለ ዘገባዎቻቸውን ያሰራጩበት ነበር። መገናኛ ብዙሃኑ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ሃገሪቷን ያጣቀሱ መረጃዎችን በዜናዎቻቸውና በትንታኔዎቻቸው አምዶችና ድረ ገፆች ላይ በማውጣት አስነብበዋል። መገናኛ ብዙሃኑ ካነሷቸው ጉዳዮች ውስጥ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የሱዳን ተቀናቃኝ የፖለቲካ ሃይሎችን ለማደራደር ካርቱም የመገኘታቸውን ዘገባ የሚያህል ሰፊ ሽፋን ያገኘ ዘገባ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ከዚህ ቀደም ስለ ኢትዮጵያ እምብዛም ሲዘግቡ ከማይታዩት እንደ ‘ስካይ ኒውስ’ ካሉ መገናኛ ብዙሃን አንስቶ በአረብኛ ቋንቋ የሚዘግቡ መገናኛ ብዙሃን ድረስ ለጉዳዩ ሰፊ ትኩረትን ችረውት ነበር። ጉዳዩ ይህንን ያህል የሚዲያ ትኩረትን እንዴት ሊስብ ቻለ? ተብሎ ቢጠየቅ ጠያቂውን ከየዋህነት ወይም ከአትኩሮት ማነስ የሚያስቆጥርበት ነገር ሊኖር እንደማይችል የመገናኛ ብዙሃኑን የዘገባ ይዘቶችን አንድ በአንድ ማየቱ ተገቢ ይሆናል።

ሁለቱም ወገኖች ማለትም የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት እና የተቃዋሚዎች ህብረት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን የማደራደር ጥያቄ እንደተቀበሉት የዘገበው ዘ ኢስት አፍሪካ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም ለአስርተ አመታት ምንም አይነት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሳያደርጉ የቆዩትን ኤርትራና ሶማልያን እንዲሁም ኬንያን እና ሶማሊያን ያደራደሩበትን ልምድ እንደሚጠቀሙ ያለውን ግምት አስቀምጧል። ሶማሊያ ኤርትራን አልሸባብ ለተባለው አሸባሪ ቡድን እገዛ ታደርጋለች በሚል ምክንያት ለተጠቀሱት አመታት ሁለቱ ሃገራት ግንኙነታቸው ሻክሮ ቆይቶ ነበር፤ ከዚያም ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለቱ መሪዎች በሞቃዲሾ ተገናኝተው እንዲወያዩ በማድረግ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የማሸማገል ጥረት ትልቅ ሚና እንደነበረው ዘኢስት አፍሪካን አንስቷል። በሌላም በኩል ሶማሊያና ኬንያ የባህር ላይ ድንበር ይገባኛል በሚል ግንኙነታቸው እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም ለዚህ ውዝግብ መርገብም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልካም የማደራደር ስራን ሰርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሱዳን ችግር ፖለቲካዊ መፍትሄን ያገኝ ዘንድ የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የወቅቱ ሊቀመንበርነት ሃላፊነታቸውን እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት የሰጣቸውን ተልዕኮ ተጠቅመው ሁለቱን አካላት የማደራደር ተግባሩን ጀምረውታል ያለው ዘ ኢስት አፍሪካ፤ የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት መሪ አብዱልፈታህ አል-ቡርሃን እና የተቃዋሚ ሀይሎች አመራሮችን ማነጋገራቸውን ፅፏል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም የአካባቢውን ሰላም ከመመለስ እንዲሁም የሱዳንን ሰላምና አንድነት ዳግም እንዲመጣ ከማድረግ አንፃር ኢትዮጵያ ጥረቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል መግለፃቸውንም ዘገባው አስነብቧል።

አራቢ 21 ዶት ኮም የተሰኘው ድረ ገፅ በበኩሉ እስካሁን ድረስ የመን፣ ሊቢያ፣ ሶሪያ፣ ግብፅና ኢራቅን ለማሸማገል የተሄደው ርቀትና ድርድሩን የመሩት አካላት ለሃገራቱ ውድቀት እንደ ምክንያት ሊነሱ እንደሚችሉ አንስቶ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሱዳን የፖለቲካ ሃይሎችን የማደራደር ውሳኔን አፍሪካዊ ለሆነው ችግር ትክክለኛ አፍሪካዊ መፍተሄን ሊያመጣ የሚችል የሚል እምነት እንደተጣለበት ሰፋ ባለው ትንታኔው አስነብቧል። ለዚህም ፅሁፉ ድርድሩ ቀለል ባለና ቅንነት በተሞላበት፣ ምንም አይነት የፖለቲካ ቁማር በሌለበት ሁኔታ ሊካሄድ እንደሚችል መታመኑንም እንደ ምክንያት አስቀምጦታል።

የሱዳንን ወቅታዊ ችግር ከመቅረፍ አንፃር በተለይ ተነሳሽነቱ ከኢትዮጵያ ለመጣበት አፍሪካዊ መፍትሄ ውጤታማነት ምንም ጥርጣሬ እንደሌለው የጠቀሰው የድረ ገፁ ፀሃፊ ለስኬታማነቱ ሶስት ቁልፍ ጉዳዮች ገፊ ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉም አንስቷል። የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሃገራቸው ህዝቦች መካከል ለዘመናት ሰፍኖ የቆየውን ጥላቻ ለማስወገድ ታሪካዊ ሊባል የሚችል እርቅና ፍቅርን ሊያጎለብቱ የሚችሉ ተግባራትን እያከናወኑ መገኘታቸው ሲሆን በሁለተኛነት ደግሞ ኢትዮጵያ የሱዳን ጎረቤት ከመሆኗ ጋር በተያያዘ የሃገሪቷ ብሄራዊ ጥቅም አንዳይጎዳ በማሰብ እንዲሁም ሶስተኛ ምክንያቱ አድርጎ ደግሞ የሁለቱ ሃገራት ጠንካራ መስተጋብራዊ ግንኙነት ሲል ጠቅሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሱዳን ፈጣን ዲሞክራሲያዊ ሽግግር እንዲመጣ ጥሪ ማቅረባቸውን በመዘገብ መረጃውን ያሰራጨው የደቡብ አፍሪካው ኤስ ኤ ቢ ሲ ኒውስ፤ የአፍሪካ ህብረት ሱዳን የሲቪል አስተዳደር እውን እስከላደረገች ድረስ የአፍሪካ ህብረት አካል እንዳልሆነች ካስታወቀበት ካለፈው ሃሙስ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካርቱም መገኘታቸውን ዘግቧል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “ ሃላፊነት የተሞላበት ፈጣን ዴሞክራሲያዊ እና ተግባቦት የተፈጠረበት የሽግግር ጊዚ እንዲሆን የጦር ሃይሉ፣ ህዝቡና የፖለቲካ ሃይሎች በርትተው ሊሰሩ ይገባል።” ሲሉ መናገራቸውንም ኤስ ኤ ቢ ሲ በዘገባው አካቷል።

የሃገሪቱ የዜና ወኪል ሱዳን ትሪቡን የሱዳን ተቃዋሚ ቡድን አመራሮች የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን የማደራደር ጥያቄ መቀበላቸውን አንስቶ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ቆይታ እንደነበራቸውም አስነብቧል። የሱዳን ተቃዋሚ ሃይሎች ለነፃነትና ለለውጥ (FFC) ከሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት (TMC) ጋር ለመደራደር ባለፈው አርብ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የዘገባው ምንጩ አፅንኦት ሰጥቶታል። ሱና የተሰኘውን የዜና ምንጭ ጠቅሶ ሱዳን ትሪቡን የወታደራዊ ሽግግር ምክር ቤቱ መሪ አል ቡርሃን “በየትኛውም ጊዜ ወደ ስምምነት ጠረዼዛው በመምጣት ለችግሩ መፍትሄ ለማምጣት ዝግጁ ነን።” ማለታቸውን አስነብቧል። የተቃዋሚ ሃይሎች በበኩሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የማደራደር ጥያቄ በመርህ ደረጃ መቀበሉን ማስታወቁንም ዘገባው አክሏል።

ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ትኩረት በማድረግ ሰፋ ያሉ የትንታኔ ዘገባዎች በማውጣት የሚታወቀው ስፑትኒክ የተሰኘው ድረ ገፅ ኢትዮጵያ በሱዳን በመቻቻል ላይ የተመሰረተ የስልጣን ክፍፍል እና ዲሚክራሲያዊ ሽግግር እንዲኖር መጠየቋን አስነብቧል። ድረ ገፁ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በስልጣን መንበር ላይ የሚገኙትን ወታደራዊ ሃላፊዎችን እንዲሁም የተቃዋሚ አመራሮችን ባገኙበት አጋጣሚ ዲሞክራሲያዊ ሽግግርን እውን ከማድረግ አንፃር ሁለቱም ወገኖች ገለልተኛ የሆነ ምክር ቤት ማቋቋም እንደሚገባቸው ነግረዋቸዋል ሲልም ፅፏል።

አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሱዳን የማደራደር ጉብኝት የዳሰሱትን ያህል የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እና ድረ ገፆች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሱዳን እስር ቤቶች ከ6 ወራት እስከ 20 አመት እስራት ተበይኖባቸው በማረሚያ ቤት የነበሩ 78 ኢትዮዽያውያንን ከእስር አስፈትተው ግባሽ ያህሉን ደግሞ ይዘው መምጣታቸውን ያለፈው ሳምንት ማገባደጃ ዘገባዎቻቸው አካል አድርገውት ነበር።