ወላድ በድባብ ትሒድ !

170

ገብረህይወት ካህሳይ ከኢዜአ

የዘንድሮውን የ10ኛ ክፍል ፈተና እንግዶችን የተቀበልንበት መልካም አጋጣሚ ነበር ። በ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የመጀመሪያ ሁለት ቀናት ከተፈታኝ ወጣቶች 12 ህፃናት ተወልደዋል።

ከኢሉባቦር ዞን ቡሬ ወረዳና ከመቱ ከተማ አብዲ ቦሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፣ ከምእራብ ሀረርጌ ዞን ሶስት ትምህርት ቤቶች፣ከባሌ ዞን አጋርፋ ወረዳ ዓሊ ሁለተኛ ደረጃ ትምህረት ቤት ፣ ከወላይታ ዞን ዳሞት ፕላሳ ወረዳ ፕላስ ትምህርት ቤትና ከሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ ቃጃ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የምስራች ! ተሰምቷል ።

ከየቦታው የምስራቹን ጀባ ላሉን የኢዜአ ሪፖርተሮች ደግሞ ደግሞ ምስር ብሉ ብለናል ።

በፈተና ወቅት ምጥ እያጣደፋቸው ”በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ”እንዲሉ ጤናማ ልጆች የተገላገሉና ፈተናቸውን በፅናት የሰሩ ወጣት እህቶቻችንን እንኳን ማርያም ማረቻችሁ ! ማለትን አስቀደምንና በሽልም ታውጣችሁ ! ማለትን አስከተልን ።

በባሌ ዞን አጋርፋ ወረዳ ትናንት ምሽቱን ወልዳ ያደረች ወጣት ዛሬ በዓሊ ሁለተኛ ደረጃ ትምህረት ቤት ተገኝታ የ10ኛ ክፍል መልቀቀቂያ ብሔራዊ ፈተናዋን በተረጋጋ ሁኔታ መውሰዷን የሮቤ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽህፈት ከሰጠው ማብራሪያ ለማወቅ ተችሏል ። የመጀመሪያው ቀን ፈተና በሰላም ስትሰራ ውላ ማታውኑ መውለዷንና በማግስቱ በፅናት ለሌላ ፈተና መቀመጧን ፅህፈት ቤቱ ገልጧል ።

በጽህፈት ቤቱ የተማሪዎች ፈተና የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሞቱማ ዋቀዮ እንደተናገሩት ወጣቷ ሌሊቱን የመጀመሪያ ልጇን ወልዳ ያደረችው በሮቤ አጠቃላይ ሆስፒታል በተደረገላት የቀዶ ጥገና ህክምና ነው ።

በኢሉአባቦር ዞን ቡሬ ወረዳና በመቱ ከተማ ደግሞ በሁለቱም የፈተና ቀናት ሁለት እህቶቻችን ወሊድኑም ሆነ ፈተናውን በብቃት ተወጥተውታል ።

በመቱ አብዲ ቦሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ ወጣት አልማዝ ደረሰ ዘንድሮ ለሀገር አቀፍ ፈተና ለመቀመጥ አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቃ ብትጠባበቅም ወሯ የገባ ነፍሰጡር መሆኗ አሳስቧት ቆይቷል። ዓመቱን ሙሉ ለፈተናው ያደረገችው ዝግጅት በዚህ ምክንያት እንዲያመልጣት ባለመፍቀዷ ማታ የጀማመራትን ድካምና ምጥ ዛሬ ማለዳ በሰላም ብትገላገልም ያሰበችውን ፈተና በሆስፒታል ሆና ከመውሰድ አላስቀራትም።

“የወለድኩበትና የፈተናው እለት መገጣጠሙ አስቸጋሪ ቢሆንም ለፈተናው በቂ ዝግጅት በማድረጌ እንዲያልፈኝ አልፈለኩም” በማለትም ፅናቷን ያረጋገጠ አስተያየት ሰጥታለች ።

የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት የሚመለከታቸው አካላትም ወጣቷ ወልዳ በተኛችበት መቱ ካርል ሪፈራል ሆስፒታል አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎላት እንድፈተን ማድረጋቸው እንዳስደሰታት ምስጋና ጭምር ያካተተ አስተያየት ሰንዝራለች ።

ወጣቷ በሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎችና ለዚሁ ስራ በተመደቡ የፈተና ጣቢያ ሰራተኞች ድጋፍ አማካኝነት በሆስፒታሉ ሆኗ ቀሪ ፈተናዎች ለመውሰድ ዝግጁነቷን ተናግራለች ።በዚሁ ኢሉአባቦር ዞን ቡሬ ወረዳ በ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ሁለተኛ ቀን ላይ ራህመት ቶላ የተባለች ወጣት ከጧቱ አንድ ሰዓት ላይ ወልዳ በተኛችበት ጤና ተቋም ሆና ፈተናውን ስትወስድ ውላለች ።

የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤቶች ሀላፊ አቶ ብርሀኑ ጉታ ለኢዜአ እንደገለፁት የወጣቷ መውለድ መረጃ እንደደረሳቸው ወዲያውኑ ወደ ቦታው ፈታኞች በመላክ አስፈላጊው ድጋፍ እንድታገኝ ተደርጓል ።

በወለይታ ዞን ዳሞት ፕላሰ ወረዳ ዛሬ ጧት ፈተና ቦታ ላይ እንደደረሰች ምጥ ያጣደፋት የ10ኛ ክፍል ወጣት ተማሪ ተገቢውን እርዳታ ከተደረገላት በኋላ ፈተናውን በመውሰድ ፅናቷን አሳይታለች ።ወንድ ልጅ በሰላም የተገላገለችው ተማሪ መብራት በሌ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረጌ የተፈጥሮ ህግ ሆኖ ብወልድም ፈተናው እንዲያልፍብኝ ስለማልፈልግ እሰከ መጨረሻው ለፈተናው ዝግጁ ነኝ ብላለች ።

በምእራብ ሀረርጌ ዞን ደግሞ ከሶስት ወጣት ተፈታኞች አራት ህፃናት በሰላም ወደ ምድራችን መጥተዋል ።

በሌላ በኩል በጋምቤላ ክልል ባለፉት ሶስት ቀናት በተሰጠው የ10ኛ ክፍል ፈተና በሁለት የፈተና ጣቢያዎች 3 ሴት ተፈታኞች መውለዳቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ቶማስ የማሎ ተናግረዋል ።

ተፈታኖቹ የወለዱት በጎርገንግናበመታር የፈተና ጣቢያዎች መሆኑን የጠቆሙት ሃላፊው ተገቢውን እንክብካቤ እየተደገላቸው ፈተናቸውን እየወሰዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ትናንት ጧትበጭሮ ከተማ ከቤት ወደ ፈተና ቦታ ተረጋገታ ያመራችው ወጣት መሁባ መሃመድ ጨርጨር ትምህርት ቤት ስትደርስ ምጥ አጣድፏት መንታ ሴት ልጆችን በሰላም ተገላግላለች ።

ከወሊድ በኋላም ፈተናዋን በተረጋጋ ሁኔታ መስራቷን የዞኑ ትምህርት መምሪያ ሃላፊ ወይዘሪ መገርቱ መሀመድ ተናግረዋል ።

ወለዷ ወጣት ሙሁባ መሀመድ በሰጠችው አስተያየት በፈተና ወቅት መውለድ ተፅእኖው ቀላል ባይሆንም መንቲያ ልጆች በማግኘቴ ግን ደስተኛ ነኝ ብላለች ።

አጠገቧ የተገኙት ባለቤቷ አቶ ኑሬ አደም በበኩላቸው በአንዴ የሁለት ልጆች አባት መሆናቸውን እንዳስደሰታቸው በመግለፅ የባለቤታቸው ፅናት ግን ከሁሉም በላይ እንዳስደሰታቸው ገልፀዋል።

በዚሁ ዞን ጭሮና ዶባ ወረዳዎች የ10ኛ ክፍል ፈተና በመወሰድ ላይ የነበሩ ሁለት ወጣቶች መውለዳቸውና ከወሊድ በሃላ ፈተናውን በሰላም ማጠናቀቃቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኋላ ወይዘሮ መገርቱ መሀመድ ገልፀው ክስተቱ የሴቶችን ፅናትና ጥንካሬ የሚያመላክት ነው ብለዋል ።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን መቄት ወረዳ የቃጃ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ብርክታዊት ጌታ እሁድ ለሰኞ አጥቢያ ወልዳ ማደርዋንና በእናትዋ ድጋፍ የ20 ደቂቃ የእግር መንገድ እየተጓዘች የሁለቱን ቀናት ፈተናዎች ሰርታለች ።

የዞኑ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሃላፊና የፈተና ኮማንድ ፖስት ኮሚቴ አባል አሳዬ ተገኜ እንደገለፁት ወጣቷ ቀሪዎቹን ፈተናዎች በፅናት ለማጠናቀቅ ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች ።

እኛም ፅናታቸውን ግምት ውስጥ አስገብተን ወላድ በድባብ ትሒድ ! ብለናል ። ለሴቶቻችን ሁሉንም ዓይነት ክብርና ሙገሳ ቢሰጣቸው ያንስ ይሆን እንጂ አይበዛባቸውም ። እነዚህ የፅናት ተምሳሌት የሆኑት ወጣት ተማሪዎች የኮራንባቸው ያክል በፈተናው ሒደት አሳፋሪ ድጊት የፈፀሙ እንደነበሩም ከወደ ምስራቅ ሸዋ ተሰምቷል ።

ዓለም ጎዶሎ ናት ይባል የለ ። ያልዘሩትን ለማጨድ የቋመጡ ፣ ለርካሽ ተወዳጅነት እራሳቸውን አሳልፈው የሰጡና ለማይረባ ጥቅም ህሊናቸውን የሸጡ ሰዎችም አጋጥመዋል ።

በምሥራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ጁዶ ኮምቦልቻ ወረዳ የ10ኛ ከፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናን በተጭበረበረ መታወቂያ ካርድ ለሌሎች ሊፈተኑ የተገኙ አራት ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ እንደገለጹት ግለሰቦቹ የተያዙት ትናንት በፈተና ጣቢያዎች ገብተው የአማርኛ፣የእንግሊዝኛና የሂሳብ ትምህርት ፈተናዎችን በመስራት ላይ እንዳሉ ነው ።

ግለሰቦቹ የተያዙት ሶስቱ በጁዶ ኮምቦልቻ፣አንደኛው ደግሞ በቡልቡላ ሲሆን የ11ኛና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው ።

ግለሰቦቹ ፈተናውን ሲሰሩላቸው የነበሩት የተማሪዎች ለጊዜው የተሰወሩ ሲሆን በህገ ወጥ ተፈታኞች ላይ ምርመራው መቀጠሉን ኮማንደሩ ተናግረዋል ።

በተመሳሳይ ሁኔታም በጋምቤላ ክልል በህገወጥ መንገድ ለሌሎች ተማሪዎች ሲፈተኑ የተገኙ ስድስት ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ቶማስ የማሎ ለኢዜአ ተናግረዋል ።