የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባን ጠቀሜታ ለህብረተሰቡ በማስገንዘብ ረገድ መገናኛ ብዙሃን በትኩረት ሊሰሩ ይገባል

115
ባህር ዳር ሰኔ 1//2010 ህብረተሰቡ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባን ጠቀሜታ በውል ተገንዝቦ ተግባራዊ እንዲያደርግ የመገናኛ ብዙሃንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ የአማራ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ አስታወቀ። ኤጀንሲው  በወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ዙሪያ ለጋዜጠኞችና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ያዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በባህር ዳር ተካሄዷል፡፡ የኤጀንሲው የመረጃ ቅበላና አቅርቦት ዳይሬክተር አቶ ስዩም ሃይሉ እንደገለጹት ኤጀንሲው ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ልደት፣ ሞት፣ ጋብቻ፣ ጉዲፍቻ፣ ፍችና ልደትን ምዝገባ እያካሄደ ይገኛል። የወሳኝ  ኩነቶች ምዝገባ ኢ-ፍታዊ ተጠቃሚነትን ለማስቀረት፣ የፍትህ አስተዳደርን ቀልጣፋ ለማድረግና ኢ-ፍታዊ ሰነዶችን ለመከላከል የሚያግዝ ነው። ሰነድ-አልባ ማስረጃዎችን ለመከላከልና የተደራጀ የስታትስቲክስ መረጃ እንዲኖር ታስቦ እየተሰራ ቢሆንም የህብረተሰቡ በወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ጥቅም ላይ ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ የክልሉ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ሂደት አዝጋሚ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ''ምዝገባው ከተጀመረበት ጀምሮ እካሁን 387 ሺህ 448 በላይ ወሳኝ ኩነቶች ተመዝግበዋል፤ አሁን ያለው የክልሉ የወሳኝ ኩነት የምዝገባ ደረጃም ከአስር በመቶ አይበልጥም'' ብለዋል። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት የህብረተሰቡ ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ በየእለቱ የሚከሰቱ ኩነቶች ሊመዘገቡ ባለመቻላቸው እንደሆነ አብራርተዋል። ስለሆነም ጋዜጠኞችና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ህብረተሰቡን የመረጃው ተደራሽ በማድረግ በኩል ጠንክረው ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት አቶ ሀይሉ። ከአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የመንግስት ኩሚዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ “ኤጀንሲው ወደ ስራ ከመግባቱ በፊት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን በንቅናቄ ማሳተፍ ነበረበት ይህ ባለመሆኑ ህብረተሰቡን የማስገንዘብ ስራ  አልተሰራም” ብለዋል። ስራው ከግንዛቤ ጋር የተያያዘ በመሆኑ  ኤጀንሲው በቀጣይም ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጋር ተከታታይ ውይይት በማድረግ ስራውን በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ''ስራው የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመቅረፍና ኢ-ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማስቀረት አይነተኛ መሳሪያ ስለሆነ ትብብርን የሚሻ ነው'' ያለው ደግሞ የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ጋዜጠኛ ደሳለኝ ክንዱ ነው። የእያንዳንዱን ኩነት ምዝገባ ጥቅም ለህብረተሰቡ ማስገንዘብ የጋዜጠኛው ግዴታ መሆኑን ገልጾ ኤጀንሲውም የኩነቶችን ጠቀሜታ ለጋዜጠኞችና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በተከታታይ ማስገንዘብ እንዳለበት ጠቁሟል፡፡ በደብረታቦር ከተማ በወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አተኩሮ በተሰጠው ስልጠናም ጋዜጠኞችና የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን የስራ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም