በያዝነው ሳምንት በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ዝናብ ሰጪ የሜቲዎሮሎጂ ገፅታዎች እየተጠናከሩ ነው

59
ሰኔ 5/2011 በያዝነው ሳምንት በመደበኛ ሁኔታ በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብና መካከለኛው አካባቢዎች ላይ ዝናብ ሰጪ የሜቲዎሮሎጂ ገፅታዎች እየተጠናከሩ እንደሚገኙ የብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡ ኤጀንሲው በሰሞኑ የአየር ትንበያ ሪፖርቱ በሰሜንና በሰሜን ምሥራቅ ላይ አልፎ አልፎ ከሚኖረው መጠነኛ ዝናብ በስተቀር ደረቅና ሞቃታማ የአየር ሁኔታ ያመዝናል ሲል ጠቁሟል፡፡ በሚቀጥሉት አሥር ቀናት ለክረምት ዝናብ መፈጠር አስተዋፅኦ የሚያደርጉ የሜቲዎሮሎጂ ገፅታዎች ከቀን ወደ ቀን እየተጠናከሩ እንደሚሄዱ ስለሚጠበቅም በብዙ የሀገሪቷ ክፍሎች ላይ የተሻለ የዝናብ መጠንና ሥርጭት ሊኖር እንደሚችል የትንበያ መረጃዎቹ ይጠቁማሉ፡፡ በዚህም ከኦሮሚያ ክልል ምሥራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ ጅማ፣ ኢሉ አባቦራ፣ የሰሜንና የምዕራብ ሸዋ ዞኖች፣ ምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌ፣ አዲስ አበባ፣ ከአማራ ክልል ደግሞ ምዕራብና ምሥራቅ ጎጃም መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይኖራቸዋል፡፡ እንዲሁም የሰሜንና የደቡብ ጎንደር ዞኖች፣ ባህርዳርአካባቢ፣ ሰሜን ሸዋ፣ የትግራይ መካከለኛውና ምዕራባዊ ዞኖች፣ የጋምቤላና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የሀዲያና የጉራጌ፣ የወላይታ፣የዳውሮ፣ የጋሞጎፋና  የቤንች ማጂ ዞኖችም እንዲሁ፡፡ በተጨማሪም ከሚጠናከሩ የደመና ክምችቶች በአንዳንድ ሥፍራዎች ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ሊከሰት እንደሚችልም ኤጀንሲው በላከው መግለጫ ጠቅሷል፡፡ በሌላ በኩል የአርሲና የባሌ ዞኖች፣ ከአፋር ዞን 3 እና 5፣ ድሬዳዋ፣ ጅግጅጋና ሲቲ ዞኖች ከሚኖራቸው የተጠናከረ የደመና ሥርጭት በአንዳንድ ቦታዎቻቸው ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ፡፡ የተቀሩት የሀገሪቷ ዞኖች ግን ደረቅ ሆነው ይሰነብታሉ ብሏል ኤጀንሲው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም