በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ብቃት ያለውና የሰለጠነ በቂ የሰው ሃይል የለም

58
ሰኔ 3/2011 በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ብቃት ያለውና የሰለጠነ በቂ የሰው ሃይል እንደሌለ የሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ገለጸ። ኢንስቲትዩቱ የተመሰረተበትን 50ኛ ዓመት ክብረ በዓል ዛሬ ሲያከብር በዘርፉ ከሚገኙ የሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር ውይይት አድርጓል። የተቋሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ሃብቷን ለአለም ሊያስተዋውቅና በተገቢው ሁኔታ ሊጠቀምበት የሚችል ብቁና የሰለጠነ የሰው ሃይል የለም። ዘርፉን በማሳደግና በማበልጸግ በሆቴል ዘርፍተ ሰማርቶ አገልግሎት መስጠት የሚችል የበቃ የሰው ሃይል ማፍራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ኢንስቲትዩቱ ያለውን የሰው ሃይል እጥረት ለመሙላት እየሰራ ቢሆንም ከገበያው ፍላጎት አንጻር ብዙ እንደሚቀረው ተናግረዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው''ዘርፉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ የሚያስፈልገው የሰው ሀይል አብሮ ማደግ ይጠበቅበታል'' ብለዋል፡፡ በአገሪቱ የሆቴል ኢንዱስትሪው እያደገ የሚገኝ በመሆኑ በሚፈለገው መጠንና ኢኮኖሚው በሚችለውና በሚፈቅደው አቅም እንዲበለጽግ ለዘርፉ ትኩረት መሥጠት አለበት ብለዋል። ኢትዮጵያ በቱሪዝም ያላትን ሃብት ለመጠቀምና በመጠቀም፣ ለማልማና ለማበልጸግ በቱሪዝም ላይ ከተሰማሩ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል። ኢንስቲትዩቱ በዚህ አመት በቀንና በማታ መርሃ ግብር በአጫጭር ስልጠናዎች፣ በዲፕሎማና በዲግሪ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ያሰለጠናቸውን አንድ ሺህ ባለሙያዎችን ያስመርቃል። ኢትዮጵያም በአለም ላይ ካሉ አገሮች በቱሪዝም ዘርፍ በተለይም በተፈጥሮና በባህል የታደለችና እምቅ አቅም ያላት አገር ናት። በዚህም ከዘርፉ በአመት 43 ቢሊዮን ዶላር ገቢ የማግኘት አቅም አንዳላት መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይሁንና ምንም እንኳን አገሪቱ በርካታ የቱሪዝም ሃብቶች ያሏት ቢሆነም ከሌሎች የአፍሪካ አገራት አንጻር ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እያገኘች አይደለም። ዓለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚያመለክቱትም በዘርፉ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን በትንሹ 60 በመቶ ብቃት ያለው ሙያተኛ ያስፈልጋል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም