ለ19 ቀናት ሲካሄድ የነበረው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቀቀ

62
ሰኔ 3/2011 የጉባኤውን ውሳኔ ያነበቡት ቅዱስ ፓትርያርኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ርዕስ ሊቃነ ዻዻሳት ዘኢትዮዽያ ሊቀዻዻስ ዘአክሱም ወ እጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ሲኖዶሱ በማጠቃላያው በሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ 14 ዋና ዋና ውሳኔዋች ማሳለፉን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተከርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለ19 ቀናት ሲያካሂደው የነበረውን ጉባኤ አጠናቋል። ሲኖዶሱ በቅድስና ዋና በፈሪሐ እግዚአብሔር በምትታወቀው ኢትዮጵያ የቱሪስት መስህብነትን ምክንያት በማድረግ የአገሪቱን ታሪክ የሚቀይር፣ የዜጎችን መልካም ስነ ምግባር የሚለውጥ ህገ ተፈጥሮንና የተቀደሰውን ስርዓተ ጋብቻ የሚያበላሽ፣ በቅዱሳት መጽሐፍት ሁሉ የተወገዙ ግብረ-ሰዶማውያን ኢትዮጵያ እንዳይገቡና ቅዱሳት መካናትንም እንዳይጎበኙ ምልዓተ ጉባኤው አውግዟል። በዚህም የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን  ቅድስና የሚጎዳ ሕገ ወጥ ተግባር ለመፈጸም መቀመጫውን በአሜሪካን ሀገር ያደረገው የግብረ-ሶዶማዊያን አስገብኚ ድርጅት በመቃወም ወደ ቅድስት ሀገራችን ኢትዮጵያ አንዳይገባ፣ ቅድስት መካናትንም እንዳይጎበኝ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ማውገዙንም ተናግረዋል። ቅዱስ ሲኖዶሱ ካሳለፈው ውሳኔ መካከል የቋሚ ሲኖዶሱ ሥልጣንና የሥራ አፈጻጸም አስመልክቶ ተከሰቱ የተባሉ የሥራ አፈጻጸሞችና ታዩ የተባሉ ግድፈቶች ጉባኤው በሰፊው ተነጋግሮ በቀጣይ ማንኛውም መንፈሳዊ ሆነ ማኅበራዊ ጉዳዮች ሕገ ቤተክርስቲያንን መሠረት አድርጎ እንዲሠራ መወሰኑን ተናግረዋል። ለተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት፣ ለአብነት ትምህርት ቤቶች፣ሰው ሠራሽ አደጋ ለተከሰተባቸው አብያተ ክርስቲያናት፣ ለተፈናቀሉ ወገኖችና ለጥንታዊያን አብያተ ክርስቲያናት ማደሻ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ መወሰኑን ቅዱስ ፓትርያርኩ አስታውቀዋል። ከአገር ውጭና በአገር ውስጥ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ተከስተው የነበሩ ችግሮች በአጥኚ ልዑካን ተጣርቶ በቀረበ አጀንዳ ላይ በመነጋገር ለአብያተ ክርስቲያናቱ መፍትሔ ይሆናል የተባለ ውሳኔ ማሳለፉን ተናግረዋል። ያለ አግባብ ተወርሰው የቆዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቤቶችና ሕንፃዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ቁርጠኛ አመራር በመመለሳቸውና መንግሥት ለቤተ ክርስቲያኒቱ መብት መጠበቅ የሰጠውን ትኩረት በማድነቅ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ ምስጋና ቀርቧል። ቅዱስ ሲኖዶሱ ማኅበራዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ባሳለፈው ውሳኔ፤ መንግሥት ዜጎች እንዲቆጠሩ በያዘው መርሐ ግብር መሠረት የቤተ ክርስቲያኒቱ ተከታዮች በትክክል እንዲቆሩና ቆጠራውም በሠላም እንዲከናወንና አገራዊ ተልኮውም እንዲሳካ በየ አህጉረ ስብከቱ ትምህርት እንዲሰጥ አስፈላጊውም ክትትል እንዲደረግ የኮሚቴ አባላት እንዲሰየሙ መወሰኑንም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ሆነው በከፍተኛ ትምህርት ቤቶች በሚቆዩባቸው ዓመታት ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸው ተከብሮ፣ የእምነት ነፃነታቸው ተረጋግጦ፣ እንደ እምነታቸው ሥርዓት በዓመት ውስጥ ባሉ ሰባት አጽዋማት የመፆም መብታቸው ተጠብቆ አስፈላጊው አቅርቦት እንዲደረግላቸው ሲኖዶሱ ጠይቋል። ሃይማኖታዊ በዓላትንም በሚያከብሩበት ጊዜያት የኖረና የቆየውን ትውፊታዊ አልባሳትን የመልበስ መብታቸው እንዲጠበቅ ለኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች የቅዱስ ሲኖዶሱ ማሳሰቢያ እንዲደርሳቸው መወሰኑንም ቅዱስ ፓትርያርኩ ተናግረዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም