በአገሪቷ የሚከናወኑ የምርምር ስራዎችን ለማጠናከር የሚያስችል የምርምር ፖለሲ እየተዘጋጀ ነው

78
አዲስ አበባ ሰኔ 3/2011 በኢትዮጵያ የሚከናወኑ የምርምር ስራዎችን ለማጠናከር የሚያስችል የምርምር ፖለሲ እየተዘጋጀ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ ያዘጋጀው የምርምር ህትመቶች፣ የምርምር ስነ ምግባርና የምርምር ጆርናሎች ላይ ያተኮረ የሁለት ቀናት አውደ ጥናት ዛሬ ተከፍቷል። በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የምርምርና ምርምር ነክ ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ቢኖር እንደተናገሩት፤ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የማስፋፋት ስራዎች ተሰርተዋል። ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተልዕኮዎች አንዱ የምርምር ስራዎችን ማከናወን ቢሆንም በተቋማቱ መስፋፋት መጠን ለምርምራ ስራዎች ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶ አለመሰራቱን ገልጸዋል። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚከናወኑ ምርምሮች ላይ ያተኮረ አገር አቀፍና አንድ ወጥ ስርዓት አለመዘርጋቱንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። የምርምር ዘርፉ በከፍተኛ ትምህርት ፖለሲ ውስጥ የተካተተና በበቂ መጠን የተዳሰሰ እንዳልነበረም ጠቁመዋል። በአገሪቱ የምርምር ዘርፉን የሚከታተል ጠንካራ አደረጃጃት፣ የሰው ኃይል፣ የምርምር ስነ ምግባርና የአሰራር ስርዓት እንዳልነበረም እንዲሁ። በሚኒስቴሩ አደረጃጀት የሳይንስና ምርምር ክፍል በማደራጀትም ለምርምር ስራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን 25 በመቶ የሚሆነውን ጊዜያቸውን በምርምር እንዲያሳልፉ የሚፈቅደውን አሰራርም የተወሰኑ መምህራን ሙሉ ጊዜያቸውን በምርምር ስራ እንዲያሳልፉ በሚፈቅድ አሰራር በማሻሻል የምርምር ስራዎችን ለማጠናከር ታቅዷል። በመሆኑም ግልጽ፣ ወጥና ሁሉን አቀፍ የምርምር ፖለሲ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል። ፖሊሲው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚከናወኑ ምርምሮች ችግር ፈቺ፣ ውጤታማና ወጥ አሰራር እንዲኖራቸው ያደርጋልም ነው የተባለው። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና ኃላፊዎች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆነ ተቋማት የተሳተፉበት አውደ ጥናትም የምርምር ፖለሲ ለማዘጋጀት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ይገኙበታል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም