በቀደሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት መዝገብ በሌሉበት ክስ የተመሰረተባቸው ስምንት ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

65
ሰኔ 3/2011 በቀደሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ መሃመድ ዑመር (አብዲ ኢሌ) መዝገብ በሌሉበት ክስ የተመሰረተባቸውን 8 ሰዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን የፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ። ተካሳሾቹ ዛሬ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡ ሲሆን በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል ሶስቱ በክሱ ላይ የተመለከቱ ተከሳሾች እነርሱ አለመሆናቸውን አስረድተዋል። በአብዲ መሃመድ ዑመር መዝገብ ክስ ከተመሰረተባቸው 47 ግለሰቦች መካከል አብዛኞቹ ላይ ክሱ በሌሉበት የተመሰረተ ሲሆን ፖሊስ ተከሳሾችን ተከታትሎ በቁጥጥር ስር እያዋለ መሆኑን ለችሎቱ አስረድቷል። በዚህም 8 ተከሳሾች ለመጀመሪያ ጊዜ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን እስካሁን በቁጥጥር ስር የዋሉት ተከሳሾች ቁጥርም 15 ደርሷል። ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሎ ችሎት ያቀረባቸው 16ኛ፣ 19ኛ፣ 22ኛ፣ 25ኛ፣37ኛ፣ 39ኛ፣ 43ኛ እና 46ኛ ተከሳሾች ናቸው። ይሁንና 22ኛ፣ 43ኛ እና 46ኛ ተከሳሽነት የቀረቡ ግለሰቦች "በክሱ የተጠቀሰው ስም የእኛ አይደለም" ሲሉ አስረድተዋል። ችሎቱም ግለሰቦቹ ማንነታቸውን የሚገልጽ ሰነድና መታወቂያ ይዘው ለሰኔ 5 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል። የተከሳሽ ጠበቆች በክስ መዝገቡ 6 ሰዎች ከተያዙ ከዘጠኝ ወራት በላይ እንደሆናቸው በመግለጽ፤ ፖሊስ ያልተያዙ ሰዎችን ለመያዝ በሚል የሚጠይቀው ተጨማሪ ጊዜ የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብታቸውን እየተስተጓጓለ መሆኑን ገልጸዋል። ስለሆነም ፖሊስ ያልተያዙ ተከሳሾችን ለመያዝ በሚያደርገው ጥረት የተከሳሾች የተፋጣነ ፍትህ የማግኘት መብት እንዳይስተጓጎልና ጉዳያቸውም ተለይቶ መቅረብ እንዳለበት ጠበቆቹ ተከራክረዋል። ፖሊስ በተከሳሽነት ፍርድ ቤት ያቀረባቸው ተጠርጣሪዎች ትክክለኛ ተከሳሾች መሆን አለመሆናቸውን ማጣራትም የፖሊስና የአቃቤ ህግ ስራ እንጂ የዳኞች መሆን የለበትም ሲሉም ተቃውመዋል። አቃቤ ህግ በበኩሉ ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ምስክሮች በሰጡት ቃልና ተከሳሾች በፈጸሙትን ወንጀል መሰረት አድርጌ ነው ብሏል። ችሎቱም ለሰኔ 5 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። የአብዲ መሐመድ ዑመር አስተዳደር በሥልጣን ላይ በቆየባቸው አመታት በክልሉ የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ባወጧቸው ተደጋጋሚ ዘገባዎች ጠቁመዋል። በክልሉ የቀድሞው የእስር ቤቱ ኃላፊ ሐሰን ኢስማኤል ኢብራሂም በቅጽል ስሙ "ሐሰን ዴሬ" በቅርቡ ሶማሊያ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ውሎ ለኢትዮጵያ ተላልፎ መሰጠቱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም