በአዲስ አበባ ከ5 አመታት በፊት የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠላቸው 3 ሆስፒታሎች የሁለቱ ግንባታ አልተጀመረም

292

ሰኔ 3/2011 በአዲስ አበባ ከ5 አመታት በፊት የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠላቸው የሶስት አዳዲስ ሆስፒታሎች ግንባታ ሁለቱ ገና እንዳልተጀመረና ግንባታው የተጀመረ አንድ  ሆስፒታልም የመዘግየት ችግር እንዳለበት ተገለጸ።

የሆስፒታሎቹ ግንባታ ያለበትን ደረጃ በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአስተዳደሩ ጤናና ኮንስትራክሽን ቢሮዎች  ከፍተኛ መጓተት እንደነበረ ነው የተናገሩት።

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ አማካሪ አቶ አንተነህ ምትኩ እንዳሉት በከተማው የሆስፒታሎችን ጤና አገልግሎት ሽፋን ለማሳደግ ምንም የሆስፒታል መሰረት ልማት በሌለባቸው የቦሌ፤ የኮልፌና ንፋስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች ደረጃቸውን የጠበቁ ሶስት ሆስፒታሎችን ለመገንባን በ2007 ዓ.ም ግንቦት ወር ነበር የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠላቸው፡፡

የሚገነቡት ሆስፒታሎች ቢያንስ በአመካይ 468 የህሙማን  አልጋ እንደሚኖራቸውና ከ17 እስከ 20 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ የሚገነበ ተደርጎ የካርታ ዝግጅት እንደተሰራላቸውም  አማካሪው ተናግረዋል፡፡

የሚገነቡት ዘመናዊ ሆስፒታሎች ሊያሟሉት ስለሚገባው መሰረተ ልማቶች ከ10 ጊዜ በላይ በከፍተኛ ባለሙያዎች ደረጃ በማስተች ያለቀለት ዲዛይን እንዲዘጋጅላቸው የተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በ2009 ዓ.ም ለ3ቱ ሆስፒታሎች የግንባታ ጨረታ እንዲወጣ ቢደረግም በኮልፌና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች የሚገነቡት ሁለት ሆስፒታሎች ጨረታው ባለመሳካቱ እስካሁን ወደ ግንባታ እንዳልገቡና በአሁኑ ወቅት በቦሌ ክፍለ ከተማ ያለው ብቻ ግንባታው መጀመሩን ነው የጠቀሱት።

የሁለቱ ሆስፒታሎች  ጨረታ ሂደት በአዲስ አበባ ኮንስትራክሽን ቢሮ በኩል ለማካሄድ በሂደት ላይ እንደሚገኝና  መቼ እንደሚሆን ትክክለኛ ጊዜው እንደማይታወቅም ነው የጠቀሱት፡፡

በሆስፒታሎቹ ግንባታ ላይ የመዘግየት ችግር ማጋጠሙን የጠቀሱት አማካሪው፤ እንደ ባለቤት ጤና ቢሮ  የሚጠበቅበትን የዲዛይንና የቦታ ዝግጅት በወቅቱ እንዲጠናቀቅ አድርጓል   ብለዋል ፡፡

ግንባታውን የሚያካሂደውን ተቋራጭ ለመለየት ለሁለት ጊዜ በፌደራልና  በአዲስ አበባ  ግዥ ኤጀንሲዎች በኩል የተደረገው የጨረታ ሂደት ውድቅ እንደሆነ አስታው፤ ለግንባታዎቹ መጓተት የጨረታ  ጊዜ  መውሰድ  ከፍተኛ ችግር  እንደነበር ጠቁመዋል።

በግንባታ ላይ የሚገኘው የቦሌ አካባቢ ሆስፒታል የጨረታ ሂደትም እስከ 10 ወራት ጊዜ መውሰዱን ያነሱ ሲሆን ጨረታውን የሚያካሂዱ አካላት በከፍተኛ ደረጃ የማጓተትና ትኩረት ያለመስጠት ችግር ለመዘግየቱ ዋና ምክንያት ነው ብለዋል፡፡

አስተዳደሩ ለሆስፒታሎቹ ግንባታ ለእያንዳንዱ 3 መቶ 50 ሚሊዮን ብር፤ በድምሩ   ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ እንደተመደበ ነው አመካሪው የጠቀሱት ፡፡

በአዲስ አበባ ኮንስራክሽን ቢሮ የፕሮጀክት ጥናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ታደሰ በበኩላቸው ግንባታው የተጀመረው የቦሌ ሆስፒታል አፈጻጸሙ 7 በመቶ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፤ በተቋራጩ የግንባታ አፈጻጸም ማነስ ችግርና ከዲዛይን ማሻሻል ጋር በተያያዘ  ግንባታው መድረስ ከሚጠበቅበት 13 በመቶ አንጻር መዘግየት እየተስተዋለበት ነው ብለዋል።

በኮልፌና በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተሞች ለመገንባት የታቀዱት ሁለቱ ሆስፒታሎች ቀደም ሲል  በነበረው አሰራር የግንባታዎቹ ባለቤቶች  የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች እንደነበሩ ጠቅሰው ፤ አስተዳደሩ በቅርቡ ባወጣው አዋጅ የአዳዲስ ፕሮጀክቶች ባለቤትነት ወደ ኮንስትራክሽን ቢሮ መዛወሩን ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ ወደ ኮንስትራክሽን ቢሮ ከተዘዋወሩ ገና 15 ቀኑ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ ፤በአሁኑ ወቅት የሁለቱም ሆስፒታሎች ግንባታ የዲዛይን ስራ ተጠናቆ የጨረታ ሰነድ የመጨረሻ ዝግጅት ላይ ነው ብለዋል፡፡

የጤና ቢሮ ከጨረታ መዘግየት ጋር  ያነሳው ችግር በኮንስትራክሽን ቢሮ በኩል እንዳልሆነ የሚናገሩት አቶ ያሬድ  ስራው ለረጅም ጊዜ የነበረውና የዘገየው በጤና ቢሮ  በኩል እንደሆነም   አስረድተዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጸ በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቶች አማካሪ ድርጅት ያቀረበው የጨረታ ሰነድ ክፍተት ስለነበረበት ተስተካክሎ እንዲቀርብ መደረጉንና በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጨረታው እንደሚወጣ ጠቁመዋል፡፡

የፕሮጀክቶቹ ካርታ ወደ ቢሮው  ከተላከ  አጭር ጊዜ መሆኑን  አቶ ያሬድ ገልጸው፤ ትኩረት አልተሰጠውም በሚል በጤና ቢሮ በኩል የቀረበው ቅሬታ ትክክል አደለም  ብለዋል፡፡

የከተማው ህዝብ ከጊዜ ወደጊዜ በክፍተኛ ሁኔታ ቁጥሩ እየጨመረ በመምጣቱና ባሉት ሆስፒታሎችም አግልግሎት ፍለጋ የሚመጣው ታካሚ  ቁጥር ከአቅም በላይ በመሆኑ  ሆስፒታሎቹ  በፍጥነት ሊገነቡ እንደሚገባም አቶ አንተነህ  አንስተዋል፡፡