ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከአክሱም ከተማ ነዋሪዎች ጋር ተወያዩ

171
ሰኔ 3/2011ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዛሬ ማለዳውን በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ ተገኝተው የአክሱም ሐውልት የተጋረጠበትን አደጋ ተመልክተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝቱን ያደረጉት የአክሱም ሐውልት የተጋረጠበትን አደጋ ለመከታተል የተቋቋመው ኮሚቴ ከሳምንት በፊት ያቀረበላቸውን ጥሪ ተከትሎ ነው። ከጉብኝቱ በኋላ ከከተማዋ ነዋሪዎች በተደረገው ውይይት ነዋሪዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐውልቱ ስጋት ላይ የወደቀ መሆኑን ተረድተው በመምጣታቸው አድንቀዋል። በውይይቱ የከተማዋ ነዋሪዎች በአገራዊ ጉዳዮች፣ የአክሱም ሐውልት የተጋረጠበትን አደጋ ጨምሮ በከተማዋ አሉ የሚሉዋቸውን ችግሮች አንስተው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ተሰቶባቸዋል። ነዋሪዎቹ የአክሱም ሃውልቶች የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ቅርሶች በመሆናቸው መንግስት ትኩረት እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ሃውልቶች ላይ ለተጋረጠው አደጋ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር በሐውልቱ ዙሪያ ለመነጋገር በመምጣታቸውም ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በሌላ በኩል ለረጅም ዘመናት የዘለቀው የአክሱም ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ጥያቄ ምላሽ ሊያገኝ እንደሚገባ የጠየቁት ነዋሪዎቹ በአገሪቱ ያሉ የሰላምና የጸጥታ መደፍረስ ጉዳዮችንም ጠይቀዋል። የፌዴራል ስርዓቱን ገርስሶ አሃዳዊ ስርዓት ለመገንባት ጥረት የሚያደርጉ ኃይሎችን በተመለከተ ጥያቄ ያቀረቡት ነዋሪዎቹ መንግስት ለፌዴራል ሥርዓቱና ህገ መንግስቱ ተግባራዊነት ላይ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል። ''የመሪዎች ብቻ ግንኙነት የሚመስለው የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት እስከ ታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ድረስ ሊወርድ ይገባል'' የሚል አስተያየት ከውይይት ተፊዎች ተነስቷል። ''የፌዴራል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት (መጅሊስ) ምርጫ ግልጽነት የጎደለው ነው'' የሚል ጥያቄ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሰንዝሯል። በመገናኛ ብዙኃን በኩል የሚተላለፉ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ አሉታዊ ፕሮፖጋንዳዎች ላይ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባውም አመላክተዋል።   በሌላ በኩል የህዝብና ቤት ቆጠራ ለምን ተራዘመ? ኢህዴግ በተግባር አለ ወይ? ፣ የወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽንን በተመለከተ ከቀጣዩ አገራዊ ምርጫ አስተማማኝነት ጋር በተያያዘ ጥያቄ አንስተዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋለው የሰላም መደፍረስ ችግር ጋር በተያያዘ እና ሰላምን፣ ዴሞክራሲንና ልማትን ያመጡ ጓዶች ጥቅም መከበር አለበት የሚሉ ጥያቄዎቻቸውን አቅርበዋል።   ነዋሪዎቹ በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የተፈጸመውን የአንድ ተማሪ ህይወት ማለፍ ተግባር አውግዘው ለኢትዮጵያ አንድነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል። በመጨረሻም ለውጡን እንደግፋለን ነገር ግን ለውጡ በትክክል እንዳይሄድ የሚያደርጉ አመራሮችና አከላት ላይ እርምጃ ሊወሰድባቸው  እንደሚገባም አሳስበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከነዋሪዎቹ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ ሲሆን የአክሱም ሐውልትን በተመለከተ  የሚደረገው የቅርስ ጥገናና እና ጥበቃ ከጣሊያን መንግስት ጋር በተደረሰው ስምምነት መሰረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። የከተማዋ የውሃ ችግር በክልሉ መንግስት የሚመለስ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነገር ግን የፌደራል መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። የእስልምናጉዳዮችምክርቤት /መጅሊስ/ ምርጫ ጋር በተያያዘ የተሰራው ስራ አንድነትን የሚያጠናክር መሆኑን ጠቁመው ይህም ተለያይተው የነበሩ ወገኖችን የኡለማዎች ምክር ቤት እንደፈታው አብራርተዋል። የአገሪቱ ሰላም ጉዳይ ላይ በተመለከተ በሰጡት ምላሽ  አንዳንዶች የተጋነነ የፀጥታ ችግር እንዳለ አድርገው የሚያወሩ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት አንጻራዊ ሰላም እንዳለ ጠቅሰዋል። ግጭትን የሚፈልጉ ሃይሎች በአገሪቱ የሰላም ችግር እንዳለ በማስመሰል ነገሮችን ለማባባስ የሚሰሩ አካላትን ህዝቡ ከመንግስት  ጎን በመቆም ሊያስቆም እንደሚገባ አስገንዝበዋል። መገናኛ ብዙኃንን በተመለከተ የማስተካከያ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ የጥላቻ ንግግርን ለመግታት ህግ እየወጣ መሆኑን አመላክተው ነጻነትና ግዴታን በእኩል ለማስኬድ እየተሰራ ነውም ብለዋል። የኢትዮ-ኤርትራ እርቀ ሰላም በሚመለከት ግንኙነቱ የመሪዎቹ ብቻ ሳይሆን የህዝብ ለህዝብ መሆኑን ባላፉት ጥቂት ወራት በሁለቱ ህዝቦች የተካሄዱ በንግድ፣ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች የተካሄዱ ሁነቶችን አውስተዋል። በአገሪቱ ያሉ የልማት ስራዎችን በተመለከተም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በዚህም ችግር የነበረባቸው ፕሮጀክቶችን ለማስቀጠል የተሰራውን ሥራም ተናግዋል። በኢኮኖሚው ዘርፍ ባለፉት 11 ወራትም ከ24 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ መገኘቱንም ጠቁመዋል። አክለውም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም አካባቢ ተዘዋውሮ የመስራት መብት ያለው መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር  አብይ አንድነታችንን በስራና በመቻቻል ማስቀጠል የሚገባ መሆኑን ጠቁመው ጀግንነት ታሪክን በማደስ  አንጂ ክላሽ በመተኮስ መሆን እንደሌለበትም አሳስበዋል። ከምርጫው ጋር በተያያዘም እንደ ኢህአዴግ ምርጫው እንዲካሄድ ፍላጎት መኖሩን ጠቅሰው፥ በጉዳዩ ላይ መግባባት ላይ ለመድረስ ግን ከሁሉም ፓርቲዎች ጋር በጋራ መምከር እንደሚገባም ተናግረዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘም ቦርዱ እንደ አዲስ እየተዋቀረ በመሆኑ ውሳኔዎች በዛ በኩል እንደሚያልፉም ጠቁመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው ህገ መንግስቱ የሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆኑን እና ጥያቄ አለኝ የሚል አካል ማድመጥ ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል። በመጨረሻም በህገ መንግስቱ ላይ ጥያቄ አይነሳ ማለት ተገቢነት የለውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በዚህ ላይ ልዩነት ካለ መነጋገርና መከራከር አግባብ ነው ብለዋል በምላሻቸው።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም