በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዙ የነበሩ 17 ሰዎች ተያዙ

54
ሰመራ ሰኔ 3/2011 ከመቀሌ ተነስቶ በአፋር ጋላፊ በኩል 17 ሰዎችን በህገ ወጥ መንገድ አሳፍሮ ወደ ጅቡቲ ለማሻገር የሞከረ ሃይሩፍ የህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪ ትናንት ሌሊት በቁጥጥር ስር መዋሉን የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ ። ተሸከርካሪው በቁጥጥር ስር የዋለው ትናንት ከሌሊቱ 9፡00 ሰዓት አካባቢ ዱብቲ ወረዳ ሰርደ  ቀበሌ ሲደርስ እንደሆነ ተነግሯል ። የአፋር ክልል ፖሊሰ ኮሚሽን የወንጀል መርማሪ ዋና ሳጅን ሳልህ ሲብላሌ እንደተናገሩት ጉዞው ከትግራይ ክልልና ከምስራቅ  አማራ የተለያዩ ዞኖች በመነሳት በህገወጥ መንገድ በጅቡቲ በኩል ወደ አረብ አገር ለመሄድ የአፋር ክልልን ዋነኛ የመውጫ በር አድርጎ ለመጠቀም የታለመ ነበር ። በሰሌዳ ቁጥር  አፋ 3- 01555 ሃይሩፍ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ውጭ በመጓዝ ላይ እንዳሉ በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል 10ሩ ሴቶች ሲሆኑ የተቀሩት ወንዶች መሆናቸው  ተመልክቷል። የመኪናው አሽከርካሪ ለፌዴራል ፖሊስ ሚሌ ዲቪዥን ተላልፎ መሰጠቱንም ተናግረዋል። ህገወጥ የሰዎች ዝውውር  በዜጎች ላይ እያስከተለ ያለውን ውስብስብ ስነ-ልቦናዊና አካላዊ ጉዳት  ለመከላከልና በሀገር ገጽታ ላይ የሚያሳድረውን ችግር ለመቆጣጠር ከሚለከታቸው የፌዴራል ጸጥታ አካላት ጋር በመሆን እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል ። ዋና ሳጅን ሳልህ አንዳሉት ባለፉት 10 ወራት ውስጥ በዋናነት ከአማራና ከትግራይ ክልሎች  በአፋር ክልል  በኩል  ወደ ጅቡቲ ለመውጣት ሲሞክሩ 1 ሺህ 100  ሰዎች ተይዘው ወደ መጡበት  አካባቢ እንዲመለሱ ተደርጓል። በአሁኑ ወቅት ቁጥጥሩ እየተጠናከረ ቢመጣም  በዚያው ልክ ህገ ወጥ ዝውውሩ መልኩና ስልቱን እየለዋወጠ  ችግር ሆኖ መቀጠሉን ገልጸው ህብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሎች ጎን በመሆን አስተዋጽኦውን ሊያጠናክር እንደሚገባ አሳስበዋል      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም