በኦሮሚያ ክልል 2 ቢሊዮን ችግኝ ይተከላል

62
ግንቦት 3/2011 የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሀገራዊ ጥሪን ለማሳካት በኦሮሚያ ክልል ከ2 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን የክልሉ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ ገለጹ። ዶክተር ግርማ አመንቴ ይህን የተናገሩት በዓለም ደረጃ ለ46ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ26ኛ ጊዜ በአዳማ ከተማ በተከበረው የአካባቢ ቀን የመዝግያ ፕሮግራም ላይ በመገኘት ባስተላለፉት መልዕክት ነው። ዜጎች ህግ መንግስቱ ባጎናፀፋቸው መብት መሰረት በፅዱና ንፁህ የአየር ፀባይ ውስጥ እንዲኖሩ ለማስቻልና የአየር ብክለት ተፅዕኖን ለመቀነስ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል። በተያዘው የክረምት ወራት በክልሉ ከ2 ቢሊዮን በላይ የተለያዩ ዝሪያ ያለቸው ችግኞች እንደሚተከሉም ገልጸዋል። "ዘላቂ የልማት ግብ ከዳር ማድረስ የሚቻለው የአካባቢ ተፅዕኖን ከግምት ውስጥ ያስገባ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ማከናወን ሲቻል ነው" ያሉት አስተባባሪ ሀገሪቷ የጀመረችውን የአረንጓዴ ልማት አጠናክሮ ማስቀጠል አማራጭ ብቻ ሳይሆን ግዴታም መሆኑን አስረድተዋል ። ክልሉ ለአካባቢ አየር ብክለት ምክንያት የሆኑ በርካታ የቆዳና ሌሎች ፋብሪካዎች እንዲዘጉ ማድረጉን አስተባባሪው ጠቅሰው ህብረተሰቡ ደንን በማልማትና በመንከባከብ ለመጪው ትውልድ በተፈጥሮ የበለፀገች ሀገር ማስረከብ እንዳለበት አመልክተዋል ። "የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሀገራዊ ጥሪን ለማሳካት በችግኝ ተከላው የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ የከፍትኛ ትምህርት ተቋማት፣ ሴቶችና ወጣቶችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ይሆናሉ" ብለዋል ። የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ በበኩላቸው አካባቢን ፅዱና ለኑሮ አመቺ ለማድረግ ከፋብሪካዎችና ከቤት በሚወጡ የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻዎች አያያዝና አወጋገድ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል። በቤት ውስጥ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ላይ ሰፊው ህብረተሰብ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ በማድረግ በአካባቢ አየር ብክለት ምክንያት የሚመጣውን የደም ዝውውርና የመተንፈሻ አካላት ችግር፣ የልብ ህመም፣ የሳንባና የጉበት ካንሰር በሽታዎች ለመከላከል መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል ። ባለፉት ዓመታት በ12 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ችግኝ በመትከልና የተራቆቱ መሬቶችን በደን በመሸፈን ሀገሪቷ 8 በመቶ የደን ሽፋን እድገት እንድታስመዘግብ ለማድረግ መቻሉን ኮሚሽነሩ ጠቅሰዋል። በዚህም አጠቃላይ የሀገሪቷ የደን ሽፋን ከነበረበት 7 በመቶ ወደ 15 በመቶ ማደጉን ነው የገለጹት። "በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጨረሻ ሽፋኑ ወደ 23 በመቶ ከፍ ለማድረስ ልዩ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን እንገኛለን" ብለዋል። በዓለም ደረጃ ለ46ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ26ኛ ጊዜ በአዳማ ከተማ በተከበረው የአካባቢ ቀን ላይ በአካባቢ ጥበቃና በደን ልማት የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ አካላት እውቅና ተሰጥቷል። ኦሮሚያ፣ ትግራይና ደቡብ እውቅና ከተሰጣቸው ክልሎች መካከል ሲሆኑ በዘንድሮ ዓመት የኦሮሚያ ክልል በአካባቢ ጥበቃ የተሻለ አፈፃፀም በማስመዝገቡ የዓመቱ ልዩ ተሸላሚ ሆኗል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም