ባለኃብቶች በአርሶ አደሮች መሬት ላይ ወረራ እያደረጉ ነው

138
ሰኔ 2/2011 በመስኖ ለማልማት የሚያስፈልገው የገንዘብ ወጭ ከፍተኛ በመሆኑ መሬታቸውን ለባለኃብቶች ለማከራየት መገደዳቸውን አርሶ አደሮች ገለጹ። ግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ የእርሻ የመሬት ወረራውን ሙሉ በሙሉ ለማስቆም መንግስት የግብርና ፖሊሲዎች፣ ደንቦችና መመሪያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ ነው ብሏል። መንግስት ለመስኖ ልማት ስትራቴጂ ካወጣ ከአስር ዓመታት በላይ ቢቆጠርም ተግባራዊነቱ ውስንነት ስላለበት አርሶ አደሮችን በአግባቡ መጥቀም አልቻለም። የኢትዮጵያ መንግስት የተቀናጀ የመስኖ ልማት መርሃ ግብር ተግባራዊ ማድረግ የጀመረበት እድሜ ከሶስት ዓመት እንደማይበልጥም የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። ያም ሆኖ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ አለመቻሉን ለኢዜአ የተናገሩት የምስራቅ ሸዋ ዞን ዱግዳ ወረዳ አርሶ አደሮች፤ የመስኖ ልማት ስራዎች በባለኃብቶች መያዛቸው እነሱ ከመሬታቸው ተገቢውን ጥቅምእንዳያገኙ አድርጓቸዋል። አርሶ አደር ጀልዱ ሚደቅሳ በመስኖ ለማልማት የሚጠይቀው ወጭ ከአቅማቸው በላይ መሆኑን ይገልፃሉ። በአካባቢው እንደአፈሩ ለምነት እየታየ ሩብ ሄክታር (አንድ ቀርጥ) መሬት ከ60 እስከ 70 ሺህ ብር ወጭ እንደሚያስጣም ተገልጿል። በመሆኑም አርሶ አደሮች ይሄንን ገንዘብ አውጥቶ የማልማት አቅም በማጣታቸው መሬታቸውንለባለኃብት ለማከራትና ዝናብ ጠብቀው ለማምረት መገደዳቸውን ነግረውናል። ወጣቱ አርሶ አደር ተስፋዬ ሞላም ከባለኃብቶች ጋር በመቀራረብ ካለው የቤተሰቦቹ ሶስት ሄክታር መሬት በመስኖ የሚያለማውን አንድ ሄክታር አሳይቶናል። አርሶ አደሮች ሙሉ በሙሉ ባይባልም በራሳቸው አቅም ወይም ከባለኃብት ጋር በመቀራረብ የተወሰኑ መሬቶቻቸውን በመስኖ የሚያለሙ እንዳሉ ገልጿል። ባለኃብቶች ለተከታታይ ዓመታት በመስኖ ካለሙ በኋላም የመሬቱ ለምነት ቀንሷል በማለት ለዓመት የአንዱን ሄክታር መሬት ኪራይ ዋጋ 30 ሺህ ብር እና ከዚያበታች እንደሚገምቱባቸውም አርሶ አደሮቹ ገልጸዋል። በኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትና በተለያዩ የግብርና ስራዎች አማካሪ የሆኑት ዶክተር አበራ ደሬሳ የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች ቆቃ፣ መቂ፣ ዝዋይና ሌሎችም ዝናብ አጠር በመሆናቸው ከመደበኛ ግብርና ይልቅ ለመስኖ ልማት የተመቹ መሆናቸውን ገልጸዋል። በመሆኑም ባለኃብቶች ያለቸውን ኢኮኖሚያዊ አቅም በመጠቀም የአርሶ አደሮችን መሬት በስፋት ይከራያሉ ብለዋል። ባለኃብቶችም ከተከራዩት የመስኖ መሬት የተሻለ ምርት ለማግኘት ሲሉ ከመጠን ያለፈ የአፈር ማዳበሪያ ስለሚጠቀሙ የአፈር ለምነቱ እንደሚቀንስ ይናገራሉ ዶክተር አበራ። በመሆኑም የአካባቢውን ስነ ምህዳር ለመጠበቅና አርሶ አደሮችም ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግስት የግብርና መሳሪያዎችን መደጎምና በኩታ ገጠም እንዲያመርቱ ማበረታታት አለበት ብለዋል። ትንንሽ እርሻ ያላቸው አርሶ አደሮች ዘመናዊ የመስኖ ድጋፍ ተደርጎላቸው በኩታ ገጠም ሲያመርቱ በእውቀት ላይ የተመሰረተ መስኖ፣ ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም፤ እንዲሁም ምቹ የከባቢ አየር ስነ ምህዳር መፍጠር ያስችላልም ብለዋል። በግብርና ሚኒስቴር ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አለማየሁ ብርሃኑ በበኩላቸው መስኖ በግብርና አንዱ የአግሮ ኢኮሎጂ ስራችን ቢሆንም የመስኖ መሬት መረጃችን በዘመናዊ መንገድ ስላልተያዘ ክፍተቶች ይኖራሉ ብለዋል። በተለይ ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ባለኃብቶች አርሶ አደሮችን በትንሽ ጥቅም በማታለል ከፍተኛ የመሬት ወረራ ይፈጽሙ እንደነበር አልሸሸጉም። የመሬት ወረራው አሁንም ሙሉ በሙሉ ባለመቆሙም መንግስት የግብርና ፖሊሲዎች፣ ደንቦችና መመሪያዎችን ተከትሎ አርሶ አደሮች የመሬታቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል ብለዋል። የማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርና ሌሎች የግብርና ግብዓት የአቅርቦትና የጥራት ችግር የነበረባቸው መሆኑን የገለጹት አቶ አለማየሁ፤ አገልግሎቱን በማዘመን አርሶ አደሮች በመሬታቸው የመስኖ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚሰራም ተናግረዋል። በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት በመላ ሀገሪቷ ከሶስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት 511 ሚሊዮን ኩንታል ምርት በመስኖ ለማልማት እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም