ከቀዝቃዛው ጦርነት እስከ ሽብር ጡዘት

204

ደሳለኝ ካሳ /ኢዜአ/

  በጥይት ጩ ት፣ በቦንብ ፍንዳታ፤ በታጣቂዎች ትርምስ፣ በሰላም አስከባሪዎች ትንቅንቅ  የሚታመሰው ቀጠና!። ከሽምቅ ውጊያ እስከ ግንባር ጦርነት፣ ከቀዝቃዘው ጦርነት እስከ ሽብር ጡዘት ታሪካዊ ክዋኔዎችን አስተናግዷል፤ እያስተናገደም ነው፡፡ በቀይ ባህርና በህንድ ውቅያኖስ  ሳንባ የሚተነፍሰው ክፍለ አህጉር፡- የአፍሪካ ቀንድ !!! ኢትዮያጵ፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳንና ኡጋንዳን በማካተት ሰባት ሀገራትን የሚያቀፈው ቀጠናው አዲሲቷ  ሀገር ደቡብ ሱዳን ጨምሮ ሶማሊላንድ እንደ ሀገር እውቅና  ካገኘች የሃገራቱ ቁጥር ወደ 9 እንደሚያሻቅብ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ቀጠናው ባለው በሁለተናዊ መስተጋብሩና  ስትራቴጂካዊነት ጠቀሜታው ከበርካታ ዘመናት ጀምሮ ዛሬም ድረስ የብዙዎችን የፖለቲካ ተንታኞችንም ሆነ ፖለቲከኞችን ትኩረት መሳቡ አልቀረም፡፡ እንደ አሜሪካ፣ ቻይና ና ሩሲያ ሃገራት ለአፍታም ቢሆን አይናቸውን ከቀጠናው አይነቅሉም፤ አለፍ ሲልም በሃገራቱ ላይ የበላይነትን ለመቀዳጀት ሲተናነቁና ሲሻኮቱ ይስተዋላሉ እንጂ፡፡ በዚህ  ጉዳይ ጥናት ካደረጉ የፖለቲካ ተንታኞች  መካከል ፤ “ለመሆኑ የአፍሪካ  ቀንድ  ለምን ልዩ ገጽታ ሊኖረቸው ቻለ ?” በሚል እኤአ 2013 ጥናት ያደረጉት ክሪስቶፈረ ክላፋም ይገኙበታል፡፡ ሀሳባቸውን በጥያቄ አሃዱ ብለው የጀመሩት ክላፋም  ውስብስቡ የአፍሪካ ቀንድ ጊዜ ጠብቆ ሊፈነዳ የሚችል የተደራረበ ችግር እንዳለበት ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ በጥናታቸው ለቀጠናው ሰላም መናጋት ምክንቶች መካከል አክራሪነትና ቀዝቃዛው ጦርነት ጥሎት ያለፈውን ብዥታ በቀዳሚነት ያነሳሉ፡፡ ቀጠናው የክርስትና እና እስልምና ሃይማናቶች የተስፋፉበት ከመሆኑም ባለፈ መጠነ ሰፊ ጎሳ፣ ብሄር፣ ቋንቋና ባህልን ያቀፈ  እንደመሆኑ  መጠን  በሃይማኖትና በጎሳ አክራሪነት እየተፈተነ  መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ብዝሃነት የተፈጥሮ ልዩ በረከት ቢሆንም ቀኝ ገዥዎች እነዚህ ልዩነቶችን መነሻ በማድረግ በከለሏቸው ሰው ሰራሽ ድንበሮች፤ ሰው ሰራሽ ሀገራት እንዲፈጠሩ በማድረጋቸው በሀገራቱ መካከል በየጊዜው የድንበር ውዝግብ እየተነሳ ወደ ግጭት አለፍ ሲልም ወደ ለየለት ጦርነት እየገቡ የቀጠናው ሰላም  በተደጋጋሚ  እንዲናጋ ማድረጉንም  ነው ያብራሩት። ቀጠናው ለረጂም ዓመታት ሰላም የራቀው መሆኑ ደግሞ ከቀሪው የአለም ክፍል ጋር በተቃርኖ እንዲታይና ከአለም ኢኮኖሚም እንዲገለል እንዳደረገም ነው የገለጹት። በነዚህ ምክንያቶ በተለያየ ጊዜ የተለያየ ግጭት ቢኖርም ከወር በፊት በተቀሰቀሰ ግጭት ሱዳን የቀጠናው የወቅቱ አጀንዳ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የአልሽር ስልጣን መልቀቅን ተከትሎ  በወታደራዊ ምክርቤቱ ቁጥጥር ስር ያለችው ሀገር ሰላሟ እየደፈረሰ፣ ግጭቶች  እያገረሹ ሀገሪቱ  ፈተና ውስጥ ገብታለች፡፡   ቀዝቃዛው ጦርነት ከሌላው የአለም ክፍል በተለየ በቀጣናው ሀገራት ከባድ ተጽእኖ አሳርፎበታል ያሉት ክላፋም ፤ዛሬ ላይ ደግሞ የሽብር ጥቃትን በማስተናገድ ከአለም በግንባር ቀደምትነት እየተጋፈጠ  መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡ “የቀጠናው የግጭት መነሻ ስረ መሰረቶች” በሚል በአሜሪካን ጆርናል ጥናታቸውን ያሳተሙት ሙሃቢ መኮንን ደግሞ፤ በአለም ሰላም ከራቃቸው ቀጠናዎች መካከል በቀዳሚነት እንደሚጠቀስ አመላክተው በአብዛኛው በቀጠናው የሚከሰቱ ግጭቶች የቀይ ባህርንና የህንድ ውቅያኖስ ስራቲጂያዊ ቦታዎች፣ የነዳጅ ሃብት፣ የእርሻ ና የግጦሽ ለም መሬቶችና እንደ ናይል ወንዝ የመሰሉ የውሃ ሃብትን በበላይነት ለመቆጣጠር ከሚመነጭ ፍላጎት እንደሆነ ነው ያብራሩት፡፡ የቀይ ባህርና የህንድ ውቅያኖስ ቁልፍ ስትራቴጂያዊ ቦታዎችን በትንሹ የቀጠናው አራት ሀገራት ማለትም ኤርትራ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ ና ሱዳን ይጋሯቸዋል፡፡ ዛሬ ላይ አለም አቀፋዊ ጠቀሜታዎችም  እየጎላ  በማመላከት ፤ በተለይ የመካከለኛው ምስራቅ፣ የኤሽያ ሀገራትና ራሺያ ከአፍሪካ ጋር ለሚያካሂዱት የንግድ ልውውጥ ቀዳሚ ምርጫቸው እየሆነ መምጣቱንም ያትታሉ፡፡ የሩቅ ምስራቅ ኤሺያ ሀገራትን ጨምሮ ሌሎች የአለም ሀገራትም የነዳጅና የኤሌክትሮኒክስ ምርቶቻቸውን ወደ አፍሪካ ለማጓጓዝ የቀይ ባህርና የህንድ ውቅያኖስ ወደቦችን ምርጫቸው ስለሚያደርጉ፤ በዚህም በተቃራኒ ጎራ ከተሰለፉ ሃይሎች መካከል የሚፈጠረው የጥቅም ግጭት ለአፍሪካ ቀንድ አለመረጋጋት መንስኤ መሆኑንም ነው ያመላከቱት። ከጥቅም ግጭትም ባለፈ በቀጠናው የሚከሰተውን ጦርነት ተከትሎ፤ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ገበያ የሚደራላቸው ሀገራትም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ጦርነት እንዲቀሰቀስ እጃቸውን ስለሚያስገቡ ለቀጠናው አለመረጋጋት ሌላኛው አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳድር  አብራርተዋል። የተፈጥሮ ሃብት ሌላኛው የግጭት መነሻ መሆኑን ያመለከቱት አጥኚው፤ ደቡቡ ሱዳን ከውስጣዊ የፖለቲካ አለመረጋጋት ባለፈ እምቅ የነዳጅ ሃብቷ ከሰሜን ሱደን ጋር ወደ ግጭት  ያስገባት የነዳጅ ሃብት ነው ይላሉ፡፡ እንደ ጥናቱ ከሆነ የምስራቅና የሰሜን አፍሪካ የውሃ ማማ የሆነችው ኢትዮጵያ ደግሞ ከቅርብ ጊዜት ወደህ በውሃ ሃብቷ ላይ ተጠቃሚቷን እያሳደገች እንደሆና በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባቸው ያለው ታላቁ የኢትዮጵ ህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ሃይል ማንጫን ተከትሎ የናይል ወንዝን ቀደም ብለው መጠቀም ከጀመሩት ሀገራት ጋር በጥርጣሬ እንድትታይ አድርጓታል። እነዚህን ጥርጣሬዎች ለመፍታትም የተፋሰሱ ሀገራት ለበርካታ ጊዜያት ተደራድረዋል፤ተመካክረዋልም፤ የነበረው የሀገራቱ ውይይትም አሁን የከፋ ጥርጣሬ ይኖራል ተብሎ ባይታሰብም የስጋት ምንጭ መሆኑ ግን አይቀርም።   የቀጠናው ሀገራት ከውስጥ ብጥብጥና አለመረጋጋት ባለፈ በመካከላቸው በሚፈጠር ድንበር ዘለል ግጭት ለቀጠናው ሌላኛው ችግር መሆኑ በተለያየ ጊዜ ይጠቀሳል፡፡ ለአብነትም በ2012 ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ወደ ግጭት አምርተው እንደነበር ያስታወሰው ጥናቱ ኡጋንዳና ኬንያ፣ ኬንያና ሱዳን ደግሞ ኤልሚ ትሪያንግል በተሰኘች የጋራ ድንበር ላይ በምትገኝ ልዩ ቦታ በይገባኛል ጥያቄ እንደሚወዛገቡ በማመላከት በኢትጵያና በሱዳን መካከልም ተመሳሳይ ችግር መኖሩን ይጠቁማል፡፡           የአሜሪካና ቻይና ፍጥጫ  በቀንዱ ሀገራት ጉዳይ ላይ ከአፍሪካ ጋር ባላት የኢኮኖሚዊ አጋነት የምትታወቀው ቻይና በቀጠናው ብሎም በአፍሪካ ያላትን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ  ለማስቀጠል ወታደራዊ ሰፈር እስከመገባት ደርሳለች ፡፡ ቲሌር ሄድሊ ኢንድፔንደት በተሰኘው ድረ- ገጽ ባሰፈሩት ሃተታ ቻይና  በጅቡቲ  የገነባችው የጦር ሰፈር  እኤአ በ2017 ነሀሴ ወር ይፋ መውጣቱን ተከትሎ አሜሪካን ማስኮረፍም ሆነ ማስቆጣቱ አልቀረም፡፡ ቀደም ብላ በጅቡቲ በገነባችው የጦር ሰፈር ቀጠናውን በብቸኝነትና በበላይነት ስትቆጣጠር ለነበረችው አሜሪካ፤ ቻይና በተቀናቃኝነት ወደ ቀጠናው ማንዣበቧ በአካባቢው ውጥረት እንዲነግስ  በደረግ ችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ያደርገዋል ነው የሚሉት  ሄድ ። ሁለቱ ሃያልን ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ  በተለያየ ጎራ ከሚሰለፉ የሃገሪቱ የፖለቲካ ሃይሎች  ከበስተጀርባ በሚያደርጉት ተጽእኖ በሚከሰተው አላስፈላጊ ግጭት ለቀጠናው ሌላ እራስ ምታት  መሆኑ  እንደማይቀር ይጠቀሳል። “የአፍሪካ ቀንድ የሰላም ሂደትና የግጭት አፈታት” በሚል ጥናታቸው የቀጠናውን ስትራቴጂነት አጽንኦት ሰጥተው የዳሰሱት ደግሞ ጆን ጂኒዩቲዮህ ናቸው፡፡ የቀንዱን ቁልፍ ስትራቲጂካዊ ቦታዎች የቀይ ባህርና የህንድ ውቅያኖስን ከሚጋሩ ሃገራት መካከል ጂቡቲ፤ ኤሪትራ፣ ሶማሊና ሱዳን እንደሚገኙበት በማመላከት ወደቦቹ የአለም አቀፋዊ የንግድ መስመር በመሆናቸው ለቀጠናው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ የላቀ ድርሻ እንዳላቸውም በአጽንኦት ያስረዳሉ፡፡ ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ የመካከለኛው ምስራቅ አፍሪካ ሀገራት፣ሩሲና የኤሽያ ሃገራት ከአፍሪካ አህጉር ጋር ለሚደርጉት የንግድ ልውውጥ ቀዳሚ ምርጫቸው እንዳደረጉትም ነው ያብራሩት፡፡ ጂኒዩቲዮህ በቀጠናው ስላለው መልካም አጋጣሚ ሲያብራሩ የናይል ወንዝና ገባሮቹ 80 በመቶውን የውሃ መጠን የሚያገኙት ከዚሁ አካባቢ በመሆኑ በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ከሰፈነ አካባቢው ለግብርና ልማት አመቺ በመሆኑ ለኢኮኖሚያዊ ብልጽግና ላቅ ያለ አስተዋጽኦ እንዳለው ይገልጻሉ። የአፍሪካ ቀንድ ካለው ስትራቴጂካዊነት አንጻር ከቀሪው አለም ጋር በቀላሉ ለመገናኘት ስለሚያችል፤ ከመካከለኛው ምስራቅና የኤሽያ ሃገራት ጋር ያለውን የንግድ ልውውጥ ለማቀላጠፍና ለማሳደግ አቅም ይፈጥርለታል ነው የሚሉት፡፡ እንደ ነዳጅ ያሉ የተፈጥሮ ሃብቶች ለግጭት መነሻ የመሆናቸውን ያህል በአነስተኛ ግብርና ኑሯቸውን ለሚገፉ የቀጠናው ሃገራት ምስኪን ዜጎች ብልጽግናም ከፍ ያለ አስተዋጽኦ  ስላላቸው ሌላው መልካም አጋጣሚ መሆኑን ያብራራሉ፡፡ የጥናታቸውን ውጤት መሰረት አደርገው ለቀጠናው መረጋጋት መፍትሔ ያሏቸውን ነጥቦች አጽንኦት  ሰጥተው  አስፍረዋል፡፡ ከመፍትሔዎቹ መካከል የጉዳዩ ተዋናኞች ግጭትን አስቀድሞ መከላከል ላይ ቅድሚያ ሰጥተው መስራት እንዳለባቸውና የግጭቶችን አዝማሚያ አስቀድሞ መተንበይ የሚያስችል ስረኣት መዘርጋት እንዳለባቸው ምከረ-ሃሳባቸውን  ያመላክታሉ፡፡ የቅድመ ማስንጠቀቂያ ስርዓት መዘረጋት ግጭቱ የሚያስከትለውን ጉዳት በመለየት ችግሩ ከመከሰቱ አስቀድሞ ወደ ብጥብጥ ሳይሸጋገር ለመግታት ያስችላልና። አለምአቀፋዊና ቀጠናዊ ድርጅቶች እንደ ኢጋድ፣ አፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቀጠናውን የግጭት መነሻ ምክንያቶች በማጤን አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ  ጣልቃ በመግባት ማረጋጋት እንደሚጠበቅባቸውም ጠቁመዋል። በተለይ ደግሞ የኢጋድን (IGAD) አቅም በማጎልበት በአርብቶ አደሮች መካከል የሚኪሰቱ ግጭቶን ለመከላከል እንደሚስያችል በማመልከት፤ አፍሪካ ህብረትም ቀጠናዊ የግጭት አፈታት አቅሙን በመገንባት በቀጠናው ላይ ልዩ ፍለጎት ያላቸው የውጭች ሃይሎች በሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት የሚከሰተውን የሰላም መናጋት መከላከል ይገባል በማለትም ነው ምክረ  ሀሳባቸውን የሰጡት። በቀጠናው ባሉ ሀገራት መካከል ያሉ አወዛጋቢ የድንበር ጉዳዮችን በመፍታት በግልጽ በማስቀመጥ የመፍትሄው አካል መሆኑን፤ ከጥቂት አመታት በፊት በኢትዮጵያና በኬንያ መካከል ያለውን የድንበር ብዥታ ግልጽ ለማድርረግ የተጀመረውን እንቅስቃሴ በማሳያነት አቅርበዋል። ሌሎች ሀገራትም ከዚህ መልካም ተሞክሮ በመውስድ በዚህ ምክንያት በመካከላቸው የሚከሰተውን ግጭት መከላከል እንደሚቻልም ያስረዳሉ፡፡ በሌላ በኩል ከለውጡ ማግስት  በኢትዮጵያ ፊታውራሪነት ቀጠናውን በኢኮኖሚዊና ማህበራዊ መስተጋብር ለማዋሃድ እተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ከፍ ያለ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑ ጥርጥር  የለውም፡፡ በተለይ ደግሞ ከኤርትራ ጋር የተፈጠረው እረቀሰላም በቀጠናው የሰላም አየር እንዲነፍስ በማደርግ ረገድ ላቅ ያለ ድረሻ እንዳለው በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ እንዲሁም  ወደብ  ካላቸው የጎረቤት ሀገራት ጋርም ወደብን በጋራ አልምቶ ለመጠቀም እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ኢኮኖሚያዊ ውህደቱን የሚያፋጥን በመሆኑ ይበል የሚያሰኝ በጎ ጅምር ነውና እያልን ሁሉም የቀንዱ ሀገራት ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት  የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ካበረከቱ ቀጠናው የተረጋጋ፣ሰላማዊ ፣ በኢኮኖሚ የበለጸገ፣  ለዜጎች  ምቹና ተመራጭ  ይሆናል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም