ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በምርጫ ቦርድ ዕጩ አባላት ዙሪያ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ተወያዩ

63
ሰኔ 1/2011 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አባላት ለመለየትና ለመመልመል የተቋቋመው ኮሚቴ የሥራ ሂደቱን በተመለከተ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና  ለፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች አጭር ሪፖርት አቅርቧል። የውይይቱ ዓላማ መልማይ ኮሚቴው በትናንትናው ዕለት ይፋ ያደረጋቸውን 8 ዕጩ አባላት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ተማክረውና አስተያየት ተሰቶበት  አራት የሚሆኑ እጩዎች ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲቀርቡ ለማድረግ ነው። መልማይ ኮሚቴው ካለፈው ወር ሚያዚያ 25 ጀምሮ ወደ ስራ በመግባት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አባላት ለመለየት እንቅስቃሴ ያደረገ ሲሆን ከተጠቆሙ ሁለት መቶ ሰዎች መካከል 8 ሰዎች መስፈርቶችን አሟልተው እጩ ሆነው እንዲቀርቡ አድርጓል። በዚህ መሰረትም 1 መጋቢ ዘሪሁን መንግስቴ 2 አቶ መላኩ ስብዓት 3 አቶ ቢሸት አየለ 4 አቶ ብርሃኑ ሞገስ 5 አቶ ደሞዜ ማሞ 6 ወይዘሮ ብዙወርቅ ከተተ 7 ዶክተር ጌታሁን ካሳ 8 አቶ አበራ ደግፌ የተባሉ እጩዎችን  ለምርጫ ቦርድ አባላት ለመለየትና ለመመልመል የተቋቋመው ኮሚቴ አቅርቦ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ አስተያየት ሰተውባቸዋል። በዚህ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በቀጣይ ዓመት በሚካሄደው ምርጫ በርካታ የአገር ውስጥና የውጪ ታዛቢ የሚኖር መሆኑን ገልፀው መንግስት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቀዋል። ለዚህም መንግስት ጠንካራ የምርጫ ተቋም እንዲኖር እየሰራ ካለው ስራዎች  መካከል አንዱ ጠንካራ የቦርድ አባላት እንዲሰየሙ ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል። በዚህም የዛሬው ምክክር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርቡ እጩዎች ከመቅረባቸው በፊት ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ግብዓት ለመሰብሰብ ታስቦ መዘጋጀቱን አጽኖት ሰተውታል። የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ በቀረቡት እጩዎች ላይ የሰጡትን ሀሳብና አስተያየት ከግምት ውስጥ አስገብተው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርቡ ከፖለቲካ ፓርቲ አራት የቦርድ አባላትን እንደሚሰይሙ ተናግረዋል። በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከፖለቲካ አመራሮቹ ጋር በጋራ በመሆን በጽህፈት ቤታቸው ቅጥር ግቢ የችግኝ ተከላ አካሂደዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም