በኦሮሚያ ክልል ብሄራዊ ፈተና በቂ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ

58
አዲስ አበባ ሰኔ 1/2011 በዘንድሮው አመት የ8ኛ፣10ኛ እና 12ኛ ክፍል ተፈታኞች በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ፈተናቸውን እንዲወስዱ በቂ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ አስታውቀዋል። ፈተናው በክልሉ በሚገኙ ከ10 ሺህ በላይ ጣቢያዎች የደረሰ ሲሆን 1 ሚሊዮን 3 ሺህ 155 ተማሪዎችም ፈተናውን እንደሚወስዱ ይጠበቃል። በተደረገው ዝግጅት 42 ሺህ 327 አባላት ያሉት የፈተና ጣቢያ ኃላፊዎች፣ ሱፐርቫይዘሮችና ፈተኞች እንድሰማሩ ተደርጓል። እንደ ዶክተር ቶላ ገለፃ ማየት ለተሳናቸው ተፈታኝ ተማሪዎች በማንበብ የሚያግዟቸው መምህራን ዝግጁ ሆነው እለቱን እየተጠባበቁ ነው። በዚህ ዓመት ከሌሎች ጊዜያት በተሻለ መልኩ ለትምህርት ጥረት ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱንም ዶክተር ቶላ አስታውሰዋል። በክልሉ በወለጋና በጉጂ ዞኖች ለተወሰኑ ጊዜያት በጸጥታ ችግር ሳቢያ በመፈናቀል ተስጓጓሎ የነበረውን ትምህርት የማካካስ ስራ ቀደም ብሎ መከናወኑንም ጠቅሰዋል። በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች በሚገኙ የፈተና ጣቢያዎች የሰላም ችግር እንዳያጋጥም ከህብረተሰቡ፣ ከወላጆች፣ ከክልልና ከፌዴራል የጸጥታ አካልት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። ለዚህም በተለያዩ አካባቢዎች በቂ ስምሪት ተደርጓል ነው ያሉት። ፈተናው ያለምንም ችግር እንዲጠናቀቅ ወላጆች፣ ማህበረሰቡ፣ ተፈታኝ ተማሪዎችና የሚመለከታቸው አካላት ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩም ጥሪያቸውን አቅርበዋል። የዘንድሮው የ10 ክፍል ከሰኔ 3 እስከ 5፣ የ12 ክፍል ከሰኔ 6 እስከ 11 እና የ8 ክፍል ፈተና ከሰኔ 12 እስከ 14 ቀን 2011 ዓ.ም የሚሰጥ መሆኑ ይታወቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም