በሰሜን ወሎ ዞን ከ30 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የሰብል ዘሮች መሸፈኑ ተጠቆመ

55
ሰኔ 1/2011 በሰሜን ወሎ ዞን ቀደም ብሎ መጣል የጀመረውን ዝናብ በመጠቀም 30 ሺህ 700 ሄክታር መሬት በተለያዩ የሰብል ዘሮች መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡ በዞኑ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ አባይ መልኩ ለኢዜአ እንደገለጹት ከግንቦት ወር መግቢያ ጀምሮ እየጣለ ያለው ዝናብ ለአገዳና ለብዕር ሰብሎች ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ በመኽር ወቅት ከ239 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው እስካሁንም 231ሺህ ሄክታር ታርሶ ለዘር ሥራ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ “ተደጋግሞ ከታረሰው መሬት ውስጥም ቀድሞ መጣል የጀመረውን ዝናብ በመጠቀም የገብስ፣ በቆሎና የማሽላን ሰብሎች ጨምሮ 30 ሺህ 708 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን ተችሏል” ብለዋል፡፡ በዘር ከተሸፈነው ማሳም 7 ሺህ 307 ሄክታሩ በተሻሻለ አሰራር በመስመር መዘራቱን ገልፀዋል፡፡ አርሶ አደሮቹ እስካሁን ለተዘራው ማሳ ስድስት ሺህ 200 ኩንታል ማዳበሪያ እንደተጠቀሙም ባለሙያው አስታውቀዋል፡፡ በዚህ የመኽር ወቅት ምርታማነትን ለማሳደግም 111 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ እስካሁን 72 ሺህ ኩንታል ቀርቦ ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በራያ ቆቦ ወረዳ ቀበሌ 05 ነዋሪ አርሶ አደር ወዳጀ መንግስቱ በበኩለቸው “እየጣለ ያለው ዝናብ ለእርሻ ስራው ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል” ብለዋል፡፡ በተለይም ደጋሌት የተባለውን ማሽላና በቆሎ ለመዝራት ዝናቡ ምቹ በመሆኑ ማሳቸውን በወቅቱ በዘር መሸፈናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ በዞኑ ጋዞ ወረዳ የቀበሌ 04 ነዋሪ አርሶ አደር ደምሌ ተስፋው በበኩላቸው ግንቦት ወር በጣለው ዝናብ በአካባቢው ቀድሞ የሚዘራውንና “ግንቦቴ ገብስ” የተባለውን የዘር አይነት መዝራታቸውን ተናግረዋል፡፡ ዝናቡ ከመኽር እርሻው በተጨማሪም ለበልግ ሰብሉ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡ በጉባላፍቶ ወረዳ የቀበሌ 11 ነዋሪ አርሶ አደር ካሳ ከተማ በበኩላቸው የማዳበሪያ ችግር እንዳልገጠማቸውና ሁለት ኩንታል ማዳበሪያ ተጠቅመው ማሽላ መዝራታቸውን ተናግረዋል፡፡ በዞኑ በዘንድሮ የመኽር ወቅት በዞኑ ከሚለማው መሬትም ከ6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱ ታውቋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም