በምእራብ ሸዋ ዞን 2 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቶ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው

71
አምቦ ሰኔ1/2010 በምእራብ ሸዋ ዞን የሚገኙ አርሶ አደሮች ለዘንድሮው የመኸር እርሻ 2 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅተው ጥቅም ላይ እያዋሉ ነው። የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀም ምርታማነትን በእጥፍ ማሳደግ እንደቻሉ አርሶ አደሮቹ ገልፀዋል፡፡ በዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤት የአፈር ለምነት ማሻሻያ ቡድን መሪ አቶ ታቡ ዴሬሳ እንዳስታወቁት የተፈጥሮ ማዳበሪያው ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው በዞኑ 22 የገጠር ወረዳዎች ነው። በአርሶ አደሮች ጉልበት የተዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ካለፈው ዓመት በግማሽ ሚሊዮን ሜትር ኩብ ብልጫ አለው፡፡ የተፈጥሮ ማዳበሪያው ከ2 ሺህ ሔክታር በላይ ማሳ ለማልማት እንደሚያስችል ገልፀዋል፡፡ የተፈጥሮ ማዳበሪያ የመሬት ለምነትንና እርጥበትን ለረዥም ጊዜ ጠብቆ በማቆየት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ የተሳታፊ አርሶአደሮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ በዞኑ ኤጀርሰ-ለፎ ወረዳ የጨለለቃ ቦቤ ቀበሌ አርሶ አደር ፈይሳ ድንቁ በሰጡት አስተያየት ከሰብል ተረፈ ምርትና ፍግ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ለመስኖና  ለመኽር እርሻ ልማት እያዋሉ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተጠቅመው ካለሙት አንድ ሄክታር የበቆሎ ማሳ 80 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ጠቁመዋል። ያገኙት ምርት ቀደም ሲል ከሚሰበስቡት በእጥፍ ብልጫ ያለው ሲሆን ዘንድሮም የተሻለ ምርት ለማምረት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። የአምቦ ወረዳ ሜጢ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ድልጋሱ ቡታ በበኩላቸው የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር ቀደም ሲል ለሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ሲያወጡ የነበረውን ወጪ በግማሽ ማዳን ችለዋል። በባለሙያ ታግዘው ዘንድሮ 180 ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅተው ማሳቸው ላይ መበተናቸውን የተናገሩት ደግሞ በሊበን ጃዊ ወረዳ ሮጌ ዳኒሳ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ተስፋሁን ዳምጤ ናቸው፡፡ በምእራብ ሸዋ ባለፈው ዓመት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቶ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም