የሱዳንን ፖለቲካ ውጥረት የሚያባብሱ ውጫዊ ጣልቃ ገብነቶች ገደብ ሊደረግባቸው ይገባል- ኢጋድ

57
ግንቦት 30/2011 የሱዳን የፖለቲካዊ ውጥረትን የሚያባብሱ ውጫዊ ጣልቃ ገብነቶች ገደብ ሊደረግባቸው እንደሚገባ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን /ኢጋድ /አሳሰበ። የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት የፀጥታ ደህንነትና የሰላም ዘርፍ ዳይሬክተር ኮማንደር አበበ ሙሉነህ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የሱዳን ፖለቲካዊ ውጥረት ከወዲሁ ማስተካከል ካልተቻለ ወደባሰ ችግር ሊያመራ ይችላል። ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር ስልጣናቸውን ለመልቀቅ የተገደዱት በአገሪቷ "ስርነቀል ለውጥ ያስፈልጋል" በሚል ከታህሳስ ወር ጀምሮ በተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት ነው። የአልበሽር መንግስት በሃይል መገርሰሱን ተከትሎም ወደ ስልጣን የመጣው ወታደራዊ የላዕላይ ምክር ቤትና ሲቪሉ መካከል አለመግባባቶች ቀጥለዋል፤ ሆኑም በመካከላቸው መግባባት ተፈጥሮ አገሪቷን ማረጋጋት አልተቻለም። የፖለቲካ ውጥረቱ መቀጠሉን ተከትሎም የአፍሪካ ህብረት በኃይል ባወጣው መግለጫ ስልጣን የያዘውን መንግስት "ተቀባይነት የለውም ሲል"  አገሪቱን ከህብረቱ አባልነት አግዷል። በአሁኑ ወቅት በስልጣን ላይ የሚገኘው የሱዳን ወታደራዊ መንግስት ስልጣኑን በህዝብ ለተመረጠ መንግስት ለማስረከብ ጊዜ እንዲሰጠው የጠየቀ ሲሆን፤ በአገሪቷ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት በመኖሩ አለመረጋጋትና ግጭቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል። የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን /ኢጋድ/ አባል አገራቱን ሰብሰባ በሱዳን ፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ ምክክር በማድረግ በሱዳን እየታየ ያለውን የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለማስቆም ይሰራል ብዬ አምናለሁ ሲሉ ኮማንደር አበበ ተናግረዋል። እንደ ኮማንደር አበበ ማብራሪያ፤ ጎሮቤት አገራት ከኢጋድ ጋር በመሆን በሱዳን ላለው የፖለቲካ ሁኔታ ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጠው ማገዝ አለባቸው። በተለይም በውጭ ጣልቃ ገብነት ምክንያት አገሪቷ ወደ እርስ በርስ ግጭት እንድትገባ የሚያደርጉ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ብለዋል። በሱዳን የተፈጠረው ቀውስ በአስቸኳይ እልባት ካልተሰጠው በጎረቤት አገራት ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድር መሆኑን የጠቆሙት ኮማንደር አበበ፤ በሶማሊያ ያለው ችግር በአካባቢው እየፈጠረ ያስከተለውን ጫና ለአብነት ጠቅሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዛሬ ወደ ሱዳን የሄዱ ሲሆን ሁለቱን አካላት ለማስማማት የሚያስችል ድርድርና ውይይት እንደሚያካሄዱም ይጠበቃል። የሱዳን ላዕላይ ወታደራዊ ምክርቤቱ የልዑካን ቡድን በቅርቡ ኢትዮጵያ መጥተው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር መምከራቸው ይታወሳል። በአሁኑ ወቅት ጄኔራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃንስ የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ፕሬዝዳንት አልበሽርን ከስልጣን አውርዶ የስልጣንመንበሩን የተቆናጠጠው ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስት ስልጣኑን ለሲቪል መንግስት የሚያስረክብበትን ጊዜ ካላፋጠነ በመላው ሱዳን አዲስ የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚጠሩ የአገሪቷ የተቃውሞ መሪዎች በቅርቡ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል። ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር እንደ አውሮጳውያኑ አቆጣጠ ከ1989 ጀምሮ 30 ዓመታት አገሪቱን በፕሬዝዳንትነት መርተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም