ለፓርኩ ግብአት የሚሆን የእንስሳት ሀብትና የእንስሳት ተዋጽዕኦ ምርትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው

643

ግንቦት 30/2011 በትግራይ ክልል በግንባታ ላይ ለሚገኘው ባዕከር አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግብአት የሚሆን የእንስሳት ሀብትና የእንስሳት ተዋጽዕኦ ምርትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት አስታወቀ።

በቢሮው የሃብት እንስሳት አስተባባሪ አቶ ተስፋማሪያም አሰፋ ለኢዜአ እንዳሉት አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኩ እየተገነባ ያለው በትግራይ ምዕራባዊ ዞን ባዕከር ከተማ አቅራቢያ ነው።

የፓርኩ ግንባታ ሥራ ተጠናቆ ወደሥራ ሲገባ የሚያስፈልገውን የእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርት በስፋት ማቅረብ እንዲቻል ከወዲሁ ሥራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል።

የተሻለ ወተት አምራች የሆኑ 22 ወረዳዎችን በክልሉ ከመለየት ጀምሮ የእርሻ መሬት ለሌላቸው ወጣቶች በነፍስ ወከፍ ሁለት የወተት ላሞች መግዣ እስከ 80ሺህ ብር በብድር ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።

በእዚህም በቀጣዩ በጀት ዓመት በክልሉ 360 ሺህ ሊትር ተጨማሪ የወተት ምርት ለማምረት መታቀዱን ነው አቶ ተስፋማሪያም የገለጹት።

በተመሳሳይ በእዚሁ ዓመት ዓሣን ጨምሮ 89ሺህ ቶን ሥጋ ወደገበያ ለማቅረብና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው።

በእያንዳንዱ የገጠር ቀበሌ 800 አርሶ አደሮችን በማደራጀት የተሻሻሉ የእንስሳት ሃብት ዝርያዎችን ለማስፋፋት ቀደም ብሎ ተግባራዊ ስልጠና መሰጠቱንም አስረድተዋል።

ስልጠናው አርሶ አደሩ የእንስሳት ልማዳዊ አያያዝ ከመቀየር ባለፈ ስለ መኖ አዘገጃጀትና አቀራረብ፣ ስለ እንስሳት አያያዝና ማድለብ ሥራ ያካተተ መሆኑን ጠቁመዋል።

አቶ ተስፋማሪያም እንዳሉት በእንስሳት ሀብት ልማት ላይ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ለማድረግ ዕቅድ ተይዟል።

ባለፈው ዓመት የወተት ላም ማርባትና በሬዎችን የማድለብ ሥራ እንደጀመሩ የገለጹት ደግሞ በትግራይ ምስራቃዊ ዞን አጽቢ ወንበርታ ወረዳ የሚኖሩት አርሶ አደር ኃይለስላሴ ተስፋይ ናቸው።

በመጀመሪያው ዓመት ሥራቸው 50ሺህ ብር ገቢ ማግኘት እንደቻሉ ተናግረዋል።

በአሁኑወቅትከሌሎች አርሶአደሮች ጋር ተቀናጅተው እንዲሰሩ መደረጉ የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን ለማግኘትና እርስ በርስ ተሞክሮ ለመለዋወጥ እንደሚያስችላቸው አስረድተዋል።

በትግራይ ደቡባዊ ዞን እንዳመኾኒ ወረዳ ዕንበባ ሓያ ቀበሌየሚኖሩት አርሶአደር ዓለም በላይ በበኩላቸው ከሌሎች የአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር በመሆን የከብት ማድለብ ሥራ ለመጀመር መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ከመኖ አዘገጃጀት ጀምሮ ስለ እንስሳት አያያዝ ስልጠና እንደተሰጣቸው ጠቁመው በቀጣይም ወደሥራ ለመግባት ለእንስሳት መግዣ የብድር አቅርቦት በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማርያም ደሳለኝ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት ባዕከር አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታው እየተካሄደ ሲሆን በተያዘው ዓመት መጨረሻም ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።