ለሃገር አቀፍ ፈተናዎች በቂ ዝግጅት መደረጉን የጌዲኦ ዞን ትምህርት መምሪያ ገለጸ

79

ዲላ ግንቦት 30/2011 በሃገራዊ ክልል አቀፍ ፈተናዎች ባለፈው ዓመት የተመዘገበውን የተማሪዎች ዝቅተኛ ውጤት ለማሻሻል በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን በደቡብ ክልል የጌዲኦ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።


የዘንድሮውን ሀገራዊና ክልላዊ ፈተና ለመስጠት የተደረገው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁንም መምሪያው  አስታውቋል።

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተካልኝ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ ዘንድሮ  ለሚሰጠው ሃገር አቀፍና ክልል አቀፍ ፈተናዎች የሚደረገው ዝግጅት ተጠናቋል።

ባለፈው አመት በአጎራባች አካባቢዎች የነበረውን የጸጥታ ችግር ተከትሎ ከመማር ማስተማር አንስቶ እሰከ  ፈተና አሰጣጥ ሂደት ድረስ የትምህርት ብክነትና መቆራረጦች እንደነበሩ አስታውሰዋል።

የተማሪዎች ውጤት በተለይም በ10ኛና በ12ኛ ክፍል ሀገራዊ ፈተናዎች ዝቅተኛ እንደነበር ገልጸው በተያዘው የትምህርት ዘመን የማሳለፍ  ምጣኔን ከፍ ለማድረግ ዓመቱን ሙሉ የእረፍት ቀናትን  ጨምሮ  የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በዞኑ 26 ሺህ 152 ተማሪዎች ለሀገራዊና ክልላዊ ፈተናዎች የሚቀመጡ ሲሆን ከዚህ ውስጥም 1 ሺህ 930  ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ናቸው ብለዋል፡፡

ፈተናው በ191 የመፈተኛ ጣቢያዎች የሚሰጥ ሲሆን የፈተና ጣቢያ አስተባባሪዎችም በቂ ማብራሪያ ተሰጥቷቸው  ወደ ትምህርት ቤቶች መላካቸውን አስረድተዋል።

በፈተና ወቅትም ተማሪዎች ከኩረጃና ሃሰተኛ መልሶችን ከመቀበል እራሳቸውን በማራቅ የልፋታቸውን ውጤት  ለማግኘት መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

ለተማሪዎች ውጤት መሻሻልም ሆነ ለፈተናው ሂደት መሳካት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አተላልፈዋል፡፡

የገደብ ወረዳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህት ቤት ርእሰ-መምህር ዳዊት ተስፋዬ በበኩላቸው ሀገር አቀፍ  ፈተና የሚወስዱ  ተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በትኩረት መሰራቱን ገልጸዋል፡፡

በተያዘው አመትም በወረዳው በርካታ ተፈናቃዮች የተጠለሉበት ሁኔታ ስለነበር በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ መጠነኛ መቆራረጦች እንደነበሩ ጠቅሰዋል፡፡

ችግሩም በተማሪዎች ውጤት ላይ ተጽኖ እንዳያሳድር ሀገራዊ ፈተናዎችን መሰረት አድርጎ የማካካሻ ትምህርት መስጠቱን አብራርተዋል።

ተማሪ ኤፍና በቀለ በበኩሏ የ10ኛ ክፍል ሀገራዊ ፈተና ለመቀበል በቂ ዝግጅት ማደረጓን ገልጻለች፡፡

በትምህርት ቤቷ እገዛ መምህራን ሲሰጧቸው የቆየው የማካካሻ ትምህርት ለፈተናው ተገቢውን ዝግጅት  እንድታደርግ እንደረዳት ተናግራለች። 

በተጨማሪም ትምህርት ቤቱ አጋዥ መጽሐፍትን በማቅረብና ተጨማሪ ጊዜያትን በማስተማር ያደረገላቸው እገዛ የሚመሰገን እንደሆነም ጠቁማለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም