የተባበሩት መንግስታት የሱዳን ቢሮውን የማዛወር ዕቅድ አለኝ አለ

69

ግንቦት 29/2011 የተባበሩት መንግስታት  በሱዳን ያለውን ቢሮ የማዛወር ዕቅድ እንዳለው አስታወቀ

ሃገሪቱ አሁን ያለችበትን አለመረጋጋትና ባለፈው ሰኞ የፀጥታ ሃይሎች በተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ የወሰዱትን እርምጃ ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለጊዜውም ቢሆን  ሱዳን ያለውን ቢሮውን ማዛወር እንደሚፈልግ  ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡

“አሁን እኛ እያደረግን ያለው ለጊዜው ቢሆን ሱዳን ያለውን መስሪያ ቤታችን  ወደ ሌላ ቦታ ማዛወር ሲሆን እስካሁን ድረስ ወሳኝ ተግባራቶችን እያከናወን እንገኛለን፤ ነገር ግን የፀጥታ ችግሩ ተፅዕኖ ፈጠሮብናል” ሲሉ የቢሮው ቃል አቀባይ ፈርሃን ሃቅ መናገራቸውን  ዘገባው አመልክቷል፡፡

ቃል አቀባዩ ምን ያህል ሰራተኛ እንደሚንቅሳቀስ፣ ወዴት እንደሚሄዱ፣ መቼ እንደሚመለሱ እና በሃገሪቱም ምን ያህል ሰራተኞች እንደሚቀሩ መረጃ ከመስጠት መቆጠባቸውን ዘገባው አክሏል፡፡

ቃል አቀባዩ አክለውም ተቋሙ ወደ ሌላ ቦታ ሲዘዋወር ምንም ዓይነት ሰራተኛ ከስራ ቦታው እንደማይለቅ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚደንት አልበሽር ለወራት ተቃውሞን ሲያስተናግዱ ከቆዩ በኋላ በወታደራዊ ሀይል ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ሱዳን ወደ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ትሄዳለች ተብሎ ተጠብቆ እንደነበረም ተጠቅሷል።

ነገር ግን ጊዜያዊ ወታደራዊ ሃይልና ተቃዋሚዎች አለመግባባታቸውን ተከትሎ ሃገሪቱ ብጥብጥ ውስጥ መግባቷን ዘገባው አመልክቷል።

ከተቃዋሚዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው የህክምና ባለሙያዎች ያለፈው ሰኞ በተወሰደ እርምጃ ከ108 በላይ ንፁሃን ዜጎች ህይወታቸው ማለፉን ተናግረው ቁጥሩም ከዚህ ሊልቅ እንደሚችል መናገራቸው ተዘግቧል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም