በትራፊክ መቅጫ ትኬት ላይ የአፈቅርሻለሁ መልዕክት የፃፈው የትራፊክ ፖሊስ በህግ ሊጠየቅ ነው

92

ግንቦት 29/2011 በትራፊክ መቅጫ ትኬት ላይ የአፈቅርሻለሁ መልዕክት የፃፈው የትራፊክ ፖሊስ በህግ ሊጠየቅ እንደሆነ ተነገረ።

ነገሩ ወደ ሃገረ ዩራጋይ ይወስደናል፤ ማንኛውም ህዝብ በሚመላለስበት አውራ ጎዳና ላይ የምታማልል ጉብል ሞተረኛ በትራፊክ ፖሊሱ እይታ ውስጥ ትገባለች፤ ይላል ኦዲቲ ሴንትራል  በዘገባው፡፡

ስሙ ያልተጠቀሰው የትራፊክ ፖሊስ ሴት ሞተረኛዋን በማስቆም የትራፊክ ህጉን የተላለፈች በማስመሰል ያስቆማታል። ከዚያም በአካላዊ ቅርጿ እጅጉን እንደተደመመም ይነግራታል፤ የልጅቷን ማራኪነትም በመጨመር በትራፊክ መቅጫ ትኬቱ ላይ አድናቆቱን ጽፎ እንደሰጣትም ዘገባው ጠቅሷል፡፡

የሱን የስራ ሁኔታም በማስረዳት የሕዝብ አገልጋይ እንደሆነ በመንገር ጭምር በትኬቱ የተወሰነ ክፍል ላይ እኔ እወድሻለሁ ብሎ ፅፏል ሲል ዘገባው አስፍሯል፡፡

በወቅቱም ተክለ ሰውነቱን በማስተካከል ለማማለል ጥረት ሲያደርግ ትኬቷ መሬት ከወደቀችበት ላይ  በካሜራ እይታ ውስጥ ትወድቅና ወዲያውኑ በማህበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ትሆናለች።

ይቺ አወዛጋቢ ትኬት አለቆቹ ጋር ከደረሰች በኋላ ምርመራ የተጀመረበት ስለመሆኑ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችም ጭምር በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ አንዳንዶች ሙገሳን ሲቸሩት ሌሎች ደግሞ ስልጣኑን ተገን በማድረግ ፆታዊ ትንኮሳና የማሽኮርመም ተግባር በመፈፀሙ በህግ ሊጠየቅ ይገባል በማለት አስተያየታቸውን መስጠታቸውን ዘገባው አስፍሯል፡፡

አንዳንድ ሰዎች እሱን እንደ አብነት በመጥቀስ ከአሁን በኋላ የትራፊክ ፖሊሶችን አስፈሪ ናቸው በማለት መጥራት ጀምረዋል፡፡

የሰውየው የበላይ አለቆች በድርጊቱ በጣም በመደነቅ ምርመራ የጀመሩበት መሆኑን የኤ ቢ ሲን ሪፖርት ዋቢ በማድረግ ኦዲቲ ሴንተራል ዘገባውን አጠናቅሯል፡፡

የትራፊክ ፖሊሱ ይህንን ተግባር ህጋዊ በሆነው ሰነድ ላይ የፍቅር ደብባቤ መፃፉ ከተረጋገጠ  የትራፊክ ፖሊስነት ሥራው ሊሰናበት እንደሚችን መነገሩን ዘገባው አስቀምጧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም