ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ኡጋንዳ አቀኑ

72
አዲስ አበባ ሰኔ 1/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኡጋንዳ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ ወደ ስፍራው አቅንተዋል። ዶክተር አብይ የሁለት ቀናት ይፋዊ  የስራ ጉብኝት ለማድረግ  ወደ ስፍራው ያቀኑት በፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ግብዣ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነገ በሚካሄደው የ29ኛው የኡጋንዳ ብሄራዊ ጀግኖች በዓል ላይ ይታደማሉ። በዚሁ ወቅት ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የአገሪቷን ከፍተኛ የክብር ሜዳሊያ ሽልማት ያበረክቱላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። መጋቢት 24 ቀን 2010ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሰየሙት  ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ በጅቡቲ፣ በሱዳን፣ በኬንያ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ እና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል። በጉብኝታቸው ወቅትም ከየአገሮቹ ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነትና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፤ የየአገሮቹን ትስስር የሚያጠናክሩ ስምምነቶችም አድርገዋል። በወቅቱም በሱዳንና ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ በእስር ይገኙ የነበሩ ዜጎች ተፈተው ወደ አገራቸው እንዲመለሱም ማድረጋቸው አይዘነጋም። በአሁኑ የኡጋንዳ ጉብኝታቸው በሁለትዮሽ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ከፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ ጋር እንደሚመክሩ ተጠቁሟል። ጉብኝቱ የሁለቱን አገሮች የህዝብ ለህዝብ ትስስርና ግንኙነት የበለጠ እንደሚያጠናክርም ይታመናል። ኢትዮጵያና ኡጋንዳ በኢጋድ ጥላ ስር በደቡብ ሱዳን ሠላም ሂደትና በሶማሊያ ፀጥታ ላይ ተባብረው እየሰሩ ይገኛሉ። በተጨማሪም ሁለቱ አገሮች የሶማሌያውያንን ሰላም ለመጠበቅ የሚንቀሳቀሰው አሚሶም የመከላከያ ሃይል ማሰማራታቸውን ይታወቃል። የኡጋንዳ ብሄራዊ  ጀግኖች ቀን  እ.አ.አ 1989 ጀምሮ ለአገራቸው ነጻነት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ የተሰዉ ጀግኖቿን የምታስብበት እለት ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም