የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለጊዜው አንዲቋረጥ ተደርጓል

64

ግንቦት 28/2011 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ለጊዜው እንዲቋረጥ ውሳኔ ተላለፈ።

ውሳኔው የተላለፈው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ እንደሆነ ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በስብሰባው በፕሪሚየር ሊጉ 27ኛው ሳምንት መካሄድ የነበረበት የኢትዮጵያ ቡና እና መቐለ ሰብዓ እንደርታ ጨዋታ በጸጥታ ስጋት ምክንያት አለመካሄዱ በሊጉ ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ በጥልቀት በመወያየትና በመመርመር የተለያዩ ውሳኔዎችን ማስተላለፉን እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

በዚሁ መሰረት ኮሚቴው ቀደም ሲል የሊግ ኮሚቴው በ27ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ መርሃ ግብር እንዲደረግ የወሰነው የኢትዮጵያ ቡና እና መቐለ ሰብዓ እንደርታ ጨዋታን በመሻር ነገ ሐሙስ እነዲከሄድ ወስኖ ነበ፤ ነገ ሊካሄድ የነበረው ጨዋታም እንዲቀር ተደርጓል።

ቀጣይ የፕሪሚየር ሊግ ውድድሮች በተገቢው መንገድ እንዲካሄድ ከክለቦች ጋር እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገርና በመወያየት ዘላቂ መፍትሔ እስኪሰጥም የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ ኮሚቴው ወስኗል።

የተለያዩ ወጪዎችና ሌሎች ጉዳዮች እንዲሁም በውድድር ደንቡ መሰረት የሚጠየቁ ጥያቄዎች በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስነ ምግባር መመሪያ እና የውድድር ደንቡ  መሰረት እንዲታዩም ውሳኔ መተላለፉን ከእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም