የገበያ ዋጋ ጭማሪ በኑሯቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳሳደረባቸው የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

130
ነቀምቴ ግንቦት 30/2010 በአካባቢያቸው እየታየ ያለው የሸቀጦችና የግንባታ እቃዎች  ዋጋ ጭማሪ በኑሯቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳሳደረባቸው በነቀምቴ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ በከተማው የቀበሌ ሰባት ነዋሪ ወይዘሮ ድንቅነሽ ምትኩ ለኢዜአ እንዳሉት በከተማው በየቀኑ በሸቀጦች ላይ የሚደረገው የዋጋ ጭማሪ ሊቋቋሙት እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡ " ፓስታ፣ ማኮሮኒ፣ ሩዝና የፉርኖ ዱቄት በኪሎ ከ25 ብር በላይ እየተሸጠ ነው " ያሉት አስተያየት ሰጪው የዋጋ ጭማሪው በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በእጅጉ እየጎዳ መሆኑን አመልክተዋል ፡፡መንግስት ገበያን የማረጋጋት እርምጃ መውሰድ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ በከተማው  የ 02 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አስናቁ ዳምጠው በበኩላቸው  የፓስታ ፣ ፣ ምስር የዳቦና  የጨው ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ በማሻቀቡ መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡ በበኬ ጃማ ክፍለ ከተማ የሱቅ ነጋዴ የሆኑት አቶ አህመድ መሐመድ በሰጡት አስተያየት ሸቀጦችን ከጅምላ አከፋፋዮች በሚረከቡበት ጊዜ ዋጋ ስለሚጨምሩባቸው እነሱም ዋጋ ጨምረው ለተጠቃሚው እንደሚሸጡ ገልጸዋል፡፡ ሚስማር በኪሎ ከ38 ብር ወደ 100 ብር ፣የቤት ኪዳን ቆርቆሮ ከ140 ብር ወደ 240 ብር መጨመሩን የተናገሩት ደግሞ የከተማው ቀበሌ ዘጠኝ  ነዋሪ አቶ ፍቃዱ ገመዳ ናቸው፡፡ ብረት ደግሞ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የዋጋ ጭማሪ በማሣየቱ ምክንያት በአሁኑ ጊዜ የእንጨትና ብረታ ብረት ድርጅቶች ሥራቸውን ለማቆም መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡ በከተማው የእንጨትና ብረታ ብረት ባለቤት ወጣት ምሥጋናው  ተስፋዬ እንዳለው ከሁለት ወራት በፊት በ270 ብር ይገዛ የበረው ላሜራ ብረት አሁን 750 ብር በመግባቱና ሌሎችም  የግንባታ እቃዎች ዋጋ በመናሩ ተጠቃሚዎችም ስለማይገዙ ስራ ፈትቷል፡፡ የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ገመቺስ ድርበባ  የዋጋ ጭማሪው ችግር ለመፍታት ከነጋዴዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ በውይይቱም ወቅት  የሸቀጦች ዋጋ ዝርዝር በግልጽ ተጽፎ እንዲለጠፍና ለገዥውም ደረሰኝ መስጠት እንዳለባቸው መግባባት ላይ መደረሱን አስረድተዋል ። ስምምነቱን በመጣስ አለኣግባብ  የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ክትትል በማድረግ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድም አቶ ገመቺስ አስጠንቅቀዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም