አየር መንገዱ ሥራ ላይ ባዋልኩት መተግበሪያ የሚጠቀሙት ደንበኞች ቁጥር አነስተኛ ነው አለ

452

መቀሌ ግንቦት 27/ 2011 በኢትዮጵያ አየር መንገድ የመቐለ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት መንገደኞች ባሉበት ቦታ ሆነው ቲኬት የሚቆርጡበት መተግበሪያ ተጠቃሚዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ገለጸ።

ደንበኞች በበኩላቸው  የመተግበሪያው አጠቃቀም የተባለለትን ያህል ቀላል እንዳልሆነ ይናገራሉ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ወይዘሮ ጽጌ ገብረስላሴ ሰሞኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳሉት በቅርንጫፉ ከአንድ ዓመት በፊት የመንገደኞችን ጊዜና ገንዘብ ለመቆጠብ የተጀመረው የሞባይል መተግበሪያ ተጠቃሚዎች የሚጠበቀውን ያህል አይደሉም።

መተገበሪያው የጉዞ ትኬት መቁረጥን  አጠቃቀም ቀላል  አድርጎታል የሚሉት ኃላፊዋ፣በዚህም ቴክኖሎጂውን ጊዜና ቦታ ሳይገድበው 24 ሰዓታት ሙሉ መጠቀም ያስችላል ብለዋል።

ቴክኖሎጂውን የሚጠቀሙ መንገደኞች የ10 በመቶ ቅናሽ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም አስረድተዋል።በተለይ ወደ ውጭ የሚጓዙ መንገደኞች የ17 ከመቶ ቅናሽ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ማንበብና መፃፍ የሚችሉ ተጠቃሚዎች በሚፈልጉት ቋንቋ ተጠቅመው የተመቻቸ አገልግሎት ለማግኘት እንደሚያስችላቸውም ነው ወይዘሮ ጽጌ  ያስረዱት።

ተጠቃሚዎች መተግበሪያውን ”ጎጉል ፕሌይ” ውስጥ በመግባት ማግኘት እንደሚችሉም  ተናግረዋል።

በአዲስ ቴክኖሎጂው ከሚጠቀሙ ደንበኞች መካከል የመቀሌ ከተማ ነዋሪ አቶ ሙዑዝ ኢታይ መተግበሪያውም መጠቀም የሚቻለውበስልክ  በኩል ስለሆነ አንዳንዴ ረዥም ጊዜ ለመጠበቅ ያስገድዳል ብለዋል።

በመተግበሪያው የአየር ቲኬት መቁረጥ ዋናው ችግር የመለያ ቁጥር ከተሰጠ  በሦስት ሰዓት ውስጥ በባንክ ገንዘቡ ገቢ ካልተደረገ እንደ አዲስ ወረፋ ለመያዝ ስለሚያስገደድ አገልግሎቱ ቀላልና በአንድ ቦታ ብቻ እንደማይጠናቀቅ ተናግረዋል።

ሌተና ኮሎኔል ሰለሞን ሃብተ ማርያም የተባሉ ተገልጋይ መተግበሪያው ሁሉንም ነገር በአንድ ቦታ ስለማይጠናቀቅ  ቲኬት በአካል ቀርበው ለመቁረጥ መገደዳቸውን ገልጸዋል።

በመተግበሪያው ለመገልገል በስልክ ረዥም ጊዜ ጥበቃና እንደገና ለክፍያ ባንክ መሄድ ስለሚያስፈልግ ተመራጭ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

ደንበኞች መተገብሪያውን እንዳይጠቀሙ የሚያደርጓቸው የኔትወርክ አገልግሎት መቆራረጥና  የእውቀት ማነስ ናቸው ያሉት ደግሞ  አቶ  ክብሮም ኪዳነ የተባሉ ደንበኛ ናቸው።  

በአሁኑ ወቅት ብዙ ማህበረሰብ የአየር ጉዞ ተጠቃሚ እየሆነ ነው ያሉት አቶ ክብሮም ፣አየር መንገድ ቴክኖሎጂውን በስፋት የማስተዋወቅና የማስረዳት ሥራ ይጠበቅበታል  ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።

አየር መንገዱ በየቀኑ ከአዲስ አበባ- መቐለ  ዘጠኝ በረራዎች ያደርጋል ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 120 የውጭና 21 የአገር ውስጥ የበረራ መሥመሮች አሉት።ከተመሠረተም ከ70 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል።