የኢድ አልፈጥር በዓል በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በድምቀት ተከበረ

56

ጎባ/ጅማ/ጭሮ ግንቦት 27/2011 በህዝበ ሙስሊሙ መካከል ጥላችን የሚፍጥር መጠራጥርን በማስወገድ ለጋራ ሃገራዊ ሰላምና አንድነት ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ተጠየቀ፡፡

1ሺ 440ኛው የኢድ አልፈጥር በጎባ፣ በጅማና ጭሮ ከተሞች በታላቅ ኃይማኖታዊ ስነ-ስርዓት  እየተከበረ  ይገኛል።

በጎባ ከተማ ዛሬ ማለዳ በተካሔደው የኢድ ሶላት ላይ የነጃሺ መስጅድ ኢማም ሼህ ካሚል አልይ ባስተላለፉት መልእክት ህዝበ ሙስሊሙ በአሉን ሲያከብር የበአሉ አለማ የሆነውን ለተቸገሩ ወገኖች ካለው ላይ በማካፈል ሊሆን ይገባል።

ፆምም ሆነ ሶላት በአግባቡ ሆኖ ለፈጣሪ የሚደርሰው ሰላም ሲኖር ብቻ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በቀጣይም ህዝበ ሙስሊሙ የአካባቢው ዘላቂ ሰላም ተጠብቆ አንዲቆይ የበኩላቸውን አስተወጽኦ እንዲወጡ ተናግረዋል፡፡

የጎባ ከተማ ከንቲባ አቶ አህመድ ሀጂ በበኩላቸው “ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ዉስጥ ሲያደርግ የቆየውን  በጎ ተግባር ከረመዳን ውጭም ማስቀጠል አለበት” ብለዋል፡፡

ምዕመኑ የህዝቦችን አብሮ የመኖር እሴት ከሚሸረሽሩ ዘረኝነትና እኩይ ተግባራት ራሱን በመቆጠብ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ሃይማኖታዊ ግዴታውን በግንባር ቀደምትነት በመወጣት መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል። 

በተመሳሳይም በጭሮ ከተማ በተካሔደ የኢድ ሶላት ላይ የተገኙት የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ አብዱራህማን  አብደላ ባስተላለፉት መልዕክት ህዝበ ሙስሊሙ በጾሙ ወቅት ያሳየውን መከባበር እና መደጋግፍ ከሌሎች እምነት ተከታይ ወገኖቹ ጋር በመሆን ሊያስቀጥል ይገባል።

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቷ እየታየ ያለው ለውጥ እንዲጠናከር እና እንዲሻሻልም የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪ አቅረበዋል።

በጅማ ስታዲየም በተደረገ የኢድ ሶላት ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙ ምዕመናንና  የሃይማኖት  አባቶች ደግሞ  ሕዝበ ሙስሊሙ በጥላቻና በመጠራጠር በመካከሉ ልዩነትና ጽብ እንዳይፈጠር ሁሉም በትኩረት እንዲሰራ ጠይቀዋል። 

የከተማው ነዋሪ ሃጂ ኡመር ሰይድ በሰጡት አስትያየት እንገለጹት የዘንድሮው የረመዳን  ጾም  የተራራቀው  ሰው ሁሉ ተቀራረቦ የጾመበት ነው።

“ህዝበ ሙስሊሙም በመቀራረብ በርካታ ኃይማኖታዊና አለማዊ ጥቅም አገኝተናል” ያሉት ሃጂ ኡመር“ በቀጣይ ይህን የተገኘውን የአንድነት ቡቃያ ጸሃይ እንዳያደርቀው መጠበቅ ነው” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም