መምህራንን ጨምሮ ለ364 ነዋሪዎች የቤት መስሪያ ቦታ በዋግ ኽምራ ተሰጠ

80

ግንቦት 27/2011 በዋግ ኽምራ ዞን ዝቋላ ወረዳ በፅፅቃ ከተማ መምህራንን ጨምሮ በህብረት ስራ ማህበራት ለተደራጁ 364 ነዋሪዎች የቤት መስሪያ ቦታ መሰጠቱን የከተማው ማዘጋጃ ቤት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የጽሕፈት ቤቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መላክ ቸኮለ ለኢዜአ እንደገለፁት ከ2009 ዓ.ም ጀምረው በቤት መስሪያ ቦታ በህብረት ስራ ማህበራት ለተደራጁ 21 ማህበራት የመስሪያ ቦታ ተሰጥቷል።

በዚህም እያንዳንዱ የማህበር አባላት ከ10 ሺህ 500 ብር በላይ የረዥም ጊዜ ቁጠባ መቆጠብ መቻላቸውንም ተናግረዋል፡፡

የመስሪያ ቦታ ከተሰጣቸው መካከልም አምስቱ ማህበራት የመምህራን ማህበር መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከ3 ነጥብ 3 ሔክታር በላይ መሬት የቤት መስሪያ ቦታ በመስጠት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ያሉት ዋና  ስራ አስፈፃሚው ከነዚህ ውስጥም 92 ያህሉ መምህራን በሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት አቅራቢያ መሬት እንዲያገኙ መደረጉን አስረድተዋል።

ተደራጅተው መሬት ያላገኙ ማህበራትም በአጭር ጊዜ ውስጥ መሬት ተዘጋጅቶ እንደሚተላለፍላቸው አስታውቀው በቀጣይም ለነዋሪዎች የመሬት ፍላጎት በአግባቡ ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በፅፅቃ ከተማ የሰርካለም ታደሰ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ጎሼ አያሌው “ለረዥም ጊዜ ስንጠይቅ የነበረው የቤት መስሪያ ቦታ ዛሬ ላይ ምላሽ አግኝቷል”ብለዋል።

“በመምህርነት ሙያ በማገኛት የወር ደሞዝ ቤተሰቤን ከማስተዳደር ባለፈ ለኪራይ ቤት በወር 400 ብር ወጭ አደርጋለሁ’’ ያሉት መምህሩ የተሰጣቸውን ቦታ ላይ ቤታቸውን ገንብተው ለመኖር እንደተዘጋጁ ተናግረዋል፡፡

የቦታ ተጠቃሚ የሆኑት አቶ አለማየሁ እንደሻው በበኩላቸው ከ2009 ዓ.ም ጀምረው የሚጠበቅባቸውን ቁጠባ አጠናቀው ባለፈው አመት ጀምረው የመስሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ እንደነበር አውስተዋል፡፡

“የረዥም ጊዜ ጥያቄያችን በዛሬው እለት ምላሽ በማግኘቱ ደስተኛ ነኝ’’ ብለዋል፡፡

“ይህም በቤት ኪራይ እናወጣበት የነበረውን ገንዘብ ከማስቀረቱም ባለፈ የራሳችንን ሃብት እንድናፈራ ያስችለናል” ብለዋል፡፡

በወረዳው በዚህ ዓመት መግቢያ ለተደራጁ 70 የቤት መስሪያ ፈላጊ ሰዎች ቦታ እንደሰተሰጠ ከጽሕፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም