የድምጽ፣ የምስልና የሙዚቃ ክምችት እጥረት አለ- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻህፍት ኤጀንሲ

89

ግንቦታ 26/2011 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻህፍት ኤጀንሲ የድምጽ፣ የምስልና የሙዚቃ ክምችት እጥረት እንዳለ አስታወቀ፡፡ 

ኤጀንሲው በዛሬው እለት የተለያዩ የሙዚቃና የፊልም ባለሙያዎችንና የደራሲያን ማህበር አባላትን ያካተተ ምክክር  አድርጓል፡፡

በኤጀንሲው የጥናትና ህግ ክምችት ዳይሬክተር ወይዘሮ እስከዳር ግሩም እንዳሉት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻህፍት ኤጀንሲ ለሃገሪቱ ሀብቶችና ቅርሶች ባለ አደራ ሆኖ  እንደመቋቋሙ  በቂ የሆነ  ክምችት  የለውም፡፡

ዳይሬክተሯ አክለውም በአገር ውስጥም ሆነ ከውጪ ሃገራት በሚመጡ ጎብኚዎች እንኳ የሚጠየቀውን ነገር በሚፈለገው ደረጃ ለማሳየት የቅርሶቹ ክምችት አናሳ ነው ብለዋል፡፡

በተለይም የጥናትና ምርምር ባለሙያዎች እጥረት የተነሳ የተሰጠንን ሃላፊነት በአግባቡ የመተግበርና ያለመቀናጀት ችግሮች እንዳለባቸው የገለጹት ዳይሬክተሯ፤ በዚህ ላይም ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ አለመስራታችን ለዚሁ ችግር አጋልጦናል ብለዋል።

"ለጋራ ሃብታችን የጋራ ጥረት ያስፈልጋል" ያሉት ወይዘሮ እስከዳር፤ አዋጅ ቁጥሩ 179/91 በሚያዘው መሰረት ለሙዚቀኞችና ለተለያዩ ግለሰቦች  የስራዎቻቸውን ቅጂ የመስጠት አስገዳጅነቱን ገልጸው በአሁኑ ሰአትም እጃቸው ላይ ያሉ ስራዎችን እንዲያስረክቧቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ተሳታፊ ሙዚቀኞችና እንግዶች በበኩላቸው የተለያዩ ስራዎች  የሚገኙባቸውን  ተቋማት  በመጠቆም  እጃቸው ላይ የሚገኙትን ስራዎች እንደሚሰጧቸው ነው የተናገሩት፡፡

የቀደምት ስራዎችን የማሰባሰቡ ሂደት ላይ እንዲረዳም በአዋጅ ቁጥሩ 179/91 የተደነገገው ደንብ እንዲጸድቅ ከተሳታፊዎች ሃሳብ የቀረበ ሲሆን የሚሰጧቸውንም የቆዩ የሸክላ ሙዚቃዎችና የተለያዩ ስራዎችን በምን አይነት መልኩ እንደሚያስቀምጧቸውም ጥያቄ መሆኑን አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም