የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ውጤታማ ሆኖ ለትውልድ እንዲተላለፍ በወጣቶች ላይ መሥራት ይገባል-የአዳማ ነዋሪዎች

62

አዳማ ግንቦት 26 / 2011 የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ውጤታማ ሆኖ ለትውልድ እንዲተላለፍ በወጣቶች ላይ መሥራት እንደሚገባ በአዳማ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።

የከተማው ነዋሪዎችና የሃይማኖት አባቶች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት እንዳስረዱት ዘመናትን የተሸጋገረውን የሕዝቦች ግንኙነት ለማጠናከር ወጣቱ ትውልድ ማንነቱንና ታረኩን የሚያውቅበት ሁኔታ መመቻቸት ይኖርበታል።

በከተማው የአኢሻ መስጂድ ኢማም ሼህ ሙሐመድ ሁሴን ወጣቶች አሁን እየታደሰ ያለውን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና አንድነት ዘመን ተሸጋጋሪ የኢትዮጵያውያን ታሪክ ማሳያ መሆኑን እንዲያውቁ መደረግ እንዳለበት ይናገራሉ።

ፖለቲከኞች በፈጠሩት አሻጥር የሕዝቦች አንድነት፣አብሮነትና ፍቅር ተቀዛቅዞ እንደነበር የሚናገሩት የሃይማኖት አባት፣ አሁን በመሪዎች እየተወሰደ ያለው እርምጃ ሁሉም ራሱን እንዲፈተሽና ለአገር ግንባታ በአንድነት እንዲቆም የሚያደርግ ነውም ይላሉ።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከአጎራባች ክልሎችና ሕዝቦች ጋር የጀመረው የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርና ግንኙነት ውጤታማ እንዲሆን ከወቅታዊነት ባለፈ ለትውልድ ለማስተላለፍ በወጣቶች ላይ መሰራት እንዳለበትም ተናግረዋል።

በመንግሥታት ደረጃ የተጀመረው ግንኙነትና ትስስር በክልሉም ሆነ ከክልሉ ውጭ ከሚኖሩት ሕዝቦች ጋር ያለውን አብሮነትና አንድነት እንደሚያጠናከር የገለጹት ደግሞ የሲንቄ እናት እጅጋየሁ ተሊላ ናቸው።

የገዳ ሥርዓት ፍትህ፣እኩልነትና አንድነት ነው ያስተማረን መሆኑን አመልክተው፣ ሞጋሳ፣ጉዲፈቻና አቃፊነትን ያስተማረን ሥርዓት ተከትለን ኢትዮጵያውያን በሃይማኖት፣በዘርና በቀለም እንደማንለያይ ለወጣቱ ማስተማር ይገባል ብለዋል።

የሕዝቦችን አንድነትና ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር አባገዳዎች፣የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎች በወጣቶች ላይ መሥራትን ማስተማር ቀዳሚ አጀንዳቸው መሆን እንዳለበትም ተናግረዋል።

''ዘረኝነት፣ጥላቻና ግጭት ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ፋሽን ሊሆን አይገባም'' ያሉት አስተያየት ሰጪዋ፣''ለዘመናት አብረን እየኖርን ነው አሁንም እንቀጥላለን። ሊያባሉን የሚፈልጉ አካላት መሣሪያ ልንሆን አይገባም'' ሲሉም ተናግረዋል።

በክልሎች የተጀመረው የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከንና ኅብረተሰብ ድረስ በማውረድ ትርጉም ያለው ውጤት እንዲኖረው ማድረግ የዜጎች ኃላፊነት መሆኑን አመልክተዋል።

በመሪዎች ደረጃ የተጀመረውን ተግባር ተተኪውን ትውልድ በማስተማርና በማነፅ ማስፋት እንደሚገባ አመልክተው፣ ለሥልጣንና ለጥቅም ብለው ሕዝቡን የሚያጋጩ ኃይሎችን መታገልና ወደ ኢትዮጵያዊ ባህላቸውና ሥነ ልቡናቸው እንዲመለሱ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በአዳማ ከተማ የጠደቸ አራራ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አብዱልከሪም እስማኤል የአገር አንድነት እንዲቀጥል፣መቻቻልና መከባበር እንዲጠናከር የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።

ቤተ እምነቶችና ምዕመናን፣ወጣቶችና ሴቶች ለጥፋት የተነሱ አካላትን በማጋለጥ አንድነትን በሚያጠናከሩ የጋራ ጉዳዮቻችን ላይ ተባብረው እንዲሰሩም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ለትርፍ የሚሮጡትን የፖለቲካ ነጋዴዎች ሕዝቡ ሊገስጻቸውና ከአፍራሽ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ማድረግ እንደሚገባው የተናገሩት አቶ አብዱልከሪም፣ሕዝቡ የአብሮነት፣መቻቻልና የአንድነት ባህሉን ማስቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

የአፋር ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ ሙሐመድ ደራስ ሙሳ እንደ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና ትስስር በደም፣ባህል፣ቋንቋ፣ሃይማኖት፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቱን እንዳሚያጠናከረው እምነታቸውን ገልጸዋል።

ግንኙነቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በየደረጃው በሚገኙ የወጣቶች አደረጃጀቶችንና ሕዝባዊ ተቋማት ለማጠናከር ኃላፊነት ወስደን መሥራት አለብን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም