ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል ፈጥር በዓልን ሲያከብር የተፈጠረውን አንድነትና መቀራረብ በሚያጎላ መንገድ መሆን አለበት

177

ግንቦታ 26/2011 ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል ፈጥር በዓልን ሲያከብር የተፈጠረውን አንድነትና መቀራረብ በሚያጎላ መንገድ መሆን እንዳለበት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አሳሰበ።

የኢትዮጵያ ዑለማዎች ምክር ቤት እና የመጂሊሱ ቦርድ በጋራ የሚከበረውን የኢድ አል ፈጥር በዓል በማስመልከት ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዑለማዎች ምክር ቤት አባል መኑልከሪም ረሺድ እንዳሉት፤ በኅዝበ ሙስሊሙ ዘንድ ያለውን አንድነትና መቀራረብ ለማጎልበት የጋራ ዑለማና ቦርድ ተቋቁሟል።

ይሄም ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል ፈጥር በዓልን  በደስታ፣ በአንድነት፣  በመተሳሰብና  በፍቅር ማክበር ያስችለዋል ብለዋል።

አሏህ በመልዕክተኛው በነብዩ መሀመድ በኩል “መልካም ስራዎች ወንጀልን ያብሳሉ” እንዳሉት  በረመዷን ፆም አላስፈላጊ ንግግርና ድርጊት ፈጽሞ የተከለከለ መሆኑን ገልጸዋል።

የዘንድሮው የኢድ አል ፈጥር በዓል ሲከበርም  ደሃን በማብላትና  በማጠጣት፣  እንዲሁም የተጎዳን በመርዳት እንዲያሳልፍ አሳስበዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ ከመጥፎ ነገሮች ሁሉ ራሱን በማራቅ መልካም ስራዎችን በማከናወን በዓሉን የደስታና የአብሮነት ማድረግ ይገባልም ብለዋል።

የመጅሊሱ የቦርድ ጸሃፊ ሀጂ ከማል ሀሩን በበኩላቸው በዓሉ በአዲስ አበባ ስታዲዬም በሚከናወን የሶላት ፕሮግራም እንደሚከበር ገልጸዋል።

የጋራ ቦርድ በመቋቋሙና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መግባባት በመደረሱ ወደ ስታዲዬም የሚሄደው የእምነቱ ተከታይ ቁጥር ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችልም ጠቁመዋል።

በመሆኑም በኅዝበ ሙስሊሙ ዘንድ ያለው መቀራረብና አንድነት የበለጠ እንዲጎለብት በጥብቅ ሥነ ምግባር እንዲካሄድ ሁሉም እንዲተባበር ጠይቀዋል።