የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለመላው ሙስሊሞች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክቱን አስተላለፈ

191

አዲስ አበባ ግንቦት 26/2011 የረመዳን ወር አማኙ መልካም ባህሪያቱን ተላብሶ የፈጣሪውን ውዴታ በመሻት የልገሳና የበጎ አድራጎት ተግባራትን የሚከውንበትና አንድነቱን የሚያጠናክርበት ጊዜ መሆኑን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ።

ጉባኤው 1ሺህ 440ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል ለህዝበ ሙስሊሙ የሰላምና የጤና እንዲሆንም ነው የተመኘው።

ጉባኤው የዘንድሮውን ረመዳን ወር በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ አነሳሽነት የተጀመረው የይቅርታና የዕርቅ ሂደት ተሳክቶ ህዝበ ሙስሊሙ አንድነቱ የተጠናከረበት መሆኑ ለኢትዮጵያን ሙስሊሞች ልዩ እንደሆነም ገልጿል።

 የረመዳን የጾም ወር አማኙ መልካም ባህሪያቱን ተላብሶ የፈጣሪውን ውዴታ በመሻት የልገሳና የበጎ አድራጎት ተግባራትን የሚከውንበትና አንድነቱን የሚያጠናክርበት ጊዜ መሆኑንም ጉባኤው አብራርቷል።

ሙስሊሙ ኅብረተሰብ በዓሉን ሲያከብር በሃይማኖቱ አስተምህሮ መሰረት የተቸገሩ ወገኖቹን በማሰብና ያለውን በማካፈል መሆን እንዳለበት አስታውሶ በተለይ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በመጠለያ የሚገኙ ወገኖችን በማሰብ በአሉን እንዲያከብርም ጥሪ አቅርቧል።