ህዝበ ሙስሊሙ ኢዱን በጋራ ሰግዶ በመተሳሰብ፣ በመተዛዘንና ለሌላቸው በመስጠት እንዲያከብር ተጠየቀ

372

አዲስ አበባ ግንቦት 26/2011 ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ-አልፈጥር በዓልን በጋራ ተሰባስቦ በመስገድ፣ በመተሳሰብና በመተዛዘን እንድያከብር የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቀዳሚ ሙፈቲ ሃጂ ኡመር እንድሪስ ጥሪ አቀረቡ፡፡

የጠቅላይ ምክር ቤቱ  ፕሬዝዳንት ጥሪውን ያቀረቡት የ1 ሺህ 440ኛው የረመዳን የፆም ወር መጠናቀቁን  ተከትሎ  የሚከበረውን የኢድ-አል ፈጥር በዓልን  በማስመልከት ባስተላለፉት የመልካም ምኞት መግለጫ ነው።

ሐጂ ዑመር በዚሁ መልዕክታቸው ህዝበ ሙስሊሙ በእለተ በዓሉ ተሰባስቦ የኢድ ሰላት ከሰገደ በኋላ በመጠያየቅ፣ ያላቸው ለሌላቸው በመስጠት አብሮነታቸውን እንድያሳዩ አሳስበዋል።

ዘንድሮ የተፈጠረው አንድነት ህዝበ ሙስሊሙን ያስደሰተ መሆኑን ያስታወሱት ቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ቀደም ሲል በመለያየት በየመስጂዱ ይሰግዱ የነበሩ ወደአደባባይ በመውጣት በጋራ እንዲሰግዱ አሳስበዋል።

በዓሉ በሰላም፣ በመተዛዘንና በጋራ በመደሰት በተክቢራ (ፈጣሪን በማወደስ) እንደሚከበርም ገልጸዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወድህ በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለው እርስ በርስ መገዳደል፣ ማፈናቀልና ማሳደድ የሰው ልጆች ባህሪ ባለመሆኑ መቆም እንዳለበትም ሐጂ  ዑመር አሳስበዋል።

ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1 ሺህ 440ኛው አመተ ሂጂራ የኢድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክትም አስተላልፈዋለ።