የመከባበርና የመቻቻል እሴቶችን በማጎልበት ለአገር እድገት በጋራ መስራት ይገባናል-የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች

74

ጋምቤላግንቦት 25 /2011 በሃይማኖቶች መካከል ያሉትን የመከባበርና የመቻቻል እሴቶች በማጎልበት ለአገር እድገት በጋራ መስራት ይገባናል ሲሉ አንዳንድ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎች የኢድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ዛሬ በከተማዋ የሚገኙ የተለያዩ መስጂዶችን  ዛሬ አጽድተዋል፡፡

በጽዳቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት በክርስቲያንና በሙስሊም እምነት ተከታይ ወንድማማቾች መካከል የቆየውን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር በማጠናከር ለክልሉ ብሎም ለአገሪቱ እድገት ድርሻቸውን ይጫወታሉ፡፡

በሁለቱ ሀይማኖቶች መካከል የዘለቀውን የአብሮነት፣የመከባበርና የመቻቻል እሴቶችን በማስቀጠልና በመካከላቸው ችግር ለመፍጠር የሚጥሩ ኃይሎችን በጋራ በመመከት ለተሻለ ግንኙነት እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡

በተለይም በዕለቱ የተደረገው መስጂዶች የማጽዳት ሥራ ይህንን በተግባር ለማሳየት ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።

በቀጣይም በዓሉን አብሮ ለማሳለፍ ማቀዳቸውን አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡

ከጽዳቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ደመላሽ ተስፋዬ የጽዳቱ ዋና አላማ በሁለቱ እምነት ተከታዮች ዘንድ የቆየውን መቻቻልና የመከባበር እሴት ለማጠናከር ነው ብለዋል፡፡

በተለይም በአሁኑ ወቅት በሁለቱ እምነት ተከታዮች ዘንድ ክፍተት ለመፍጠር የሚጥሩ ኃይሎች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እንደሚስተዋሉ እነዚህን ችግሮች ለመከላከል የነበረውን ግንኙነት እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ለአገር እድገትና ልማት የምናደርገውን ጥረት አጠናክረን ለማስቀጠል በሃይማኖቶች መካከል በመቻቻልና በመከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነት በማጠናከር ልንሰራ ይገባናል ብለዋል፡፡

የጽዳት ዘመቻው የሁለቱ እምነት ተከታዮች በደስታም ሆነ በኀዘን ጊዜ ያላቸውን ማህበራዊ ግንኙነት ለማሳደግ  ፋይዳ እንዳለው የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ብቂልቱ ቢቂላ ናቸው፡፡

በዓሉን ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጋር ለማሳለፍ መዘጋጀታቸውንም አስተያየት ሰጪዋ ገልጸዋል፡፡

ሼህ ሐሩን መሐመድ የከተማዋ ነዋሪዎች የኢድ አልፈጥር ሶላትን የሚሰገድበትን ቦታ ማጽዳታቸው ከቀደሙት አባቶቻችን ጀምሮ ያለውን የመቻቻልና መከባበር እሴት ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የኢድ አል ፈጢር በዓል በሚቀጥለው ሣምንት ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም