በሃይማኖቶች መካከል ያለውን አንድነትና መተሳሰብ እንደሚያጠናክሩ ነዋሪዎቹ ገለጹ

866

አዳማ/ጅማ ግንቦት 25/2011 በሃይማኖቶች መካከል ያለውን አንድነትና መተሳሰብ በማጠናከር አኩሪ እሴቶችን ለትውልድ ለማስተላለፍ እንደሚሰሩ የአዳማና የጅማ ከተሞች የተለያዩ የእምነት ተከታዮች ገለጹ። 
በከተሞቹ የኢድ ሶላት መስገጃ ቦታዎችን ያፀዱ እምነት ተከታዮች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት የእምነት ልዩነት የማይለያየው አንድነትን ለቀጣይ ትውልዶች ለማሸጋገር ይሰራሉ።

በአዳማ ከተማ የቀበሌ 11 ነዋሪ ወይዘሮ ወርቄ ባልቻ በከተማዋ እምነት ሳይለያያቸው በአንድነት በፍቅር በመኖር ላይ መሆናቸውን ገልጸው ፣ ለሙስሊሙ ማህብረሰብ ያላቸውን ክብር ለማሳየት በሥራው መሳተፋቸውን አስታውቀዋል።

የኢድ ፀሎት የሚደረግበትን ሥፍራ ለማጽዳት የመጣሁት በሃይማኖት ሊያለያዩን የሚሞክሩ ኃይሎች እንዳልተሳካላቸውና አንድ መሆናችንን ለማሳየት ነው ያለው የደጋጋ ቀበሌ ነዋሪው ወጣት በሻዳ ገዳ ነው።

አቶ አወል ጀማል የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው በብሄርና በሃይማኖትልየቱነት ሳያግደው የተከናወነው ጽዳት   የጥላቻ  አስተሳሰብንና ተግባርን ጭምር ከውስጥ ለማውጣት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

”እኛ የሌሎችን ሃይማኖት ስናከብር የእኛም ይከበራል።በግለሰብም ሆነ በማህበረሰብ ደረጃ መከባበር ሲኖር መተሳሰብና አንድነት ይበልጥ ይጠናከራል”ብለዋል።

የተለያዩ የእምነት ተከታዮች በአንድነት ሆነው የፀሎት ቦታውን ማፅዳታቸው የኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ እሴት ማሳያ በመሆኑ ለትውልዶች ማስተላለፍ ይጠበቅብናል  ያሉት ደግሞ የአዳማ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ መሐመድ ከማል ናቸው።

በተመሳሳይ በጅማ ከተማ የረመዳን ጾም ፍችና የኢድ ሶላት መስገጃ ቦታዎች ጽዳት በተለያዩ  እምነት ተከታዮች ተከናውኗል፡፡


የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ የሆነው ወጣት ግርማ ዓለሙ የእስልምና እምነት ተከታይ ወገኖች የበዓል ማክበሪያ ጽዳት በመሳተፉ ደስታ እንደተሰማው ተናግሯል፡፡

በቀጠይ በመሰል ተግባራት በመሳተፍና ሌሎችም እንዲሳተፉ በማድረግ  ድርሻዬን እወጣለሁ ብሏል፡፡

ወጣት ሀይደር ኑረ እንደገለጸው ሕዝበ ሙስሊሙ ከሌሎች እምነት ተከታታዮች የመኖር ባህል ወደ መተሳሰብና መዋደድን ለማደጉ ዛሬ በጽዳት ዘመቻው የታየው አንድነት ማሳያ ነው ብሏል።
አቶ አባጀሃድ ጀማል በበኩላቸው የበዓሉ ማክበሪያ ቦታ የሌሎች እምነት ተከታዮችና አባቶች በመጽዳቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ መኪዩ መሐመድ  የከተማው የተለያዩ እምነት ተከታዮች ያከናወኑት ሥራ ለሕዝቦች መቀራረብ፣አንድነት፣መተሳሰብና መዋደድን የሚያመጣ ተግባር መሆኑን መስክረዋል፡፡

በቀጣይም አንዱ ለሌላው ያለውን ፍቅር በእንዲህ ዓይነት ተግባር ማሳየት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡