የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ፈተና በሰላም ተጠናቋል-ትምህርት ሚኒስቴር

73
አዲሰ አበባ ግንቦት 30/2010 ላለፉት አራት ቀናት በመላው ሀገሪቷ ሲሰጥ የቆየው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ብሄራዊ ፈተና  በሰላም መጠናቀቁን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። ካለፈው ሰኞ ግንቦት 27 ጀምሮ በተሰጠው ብሄራዊ ፈተና 284 ሺህ 558 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ተሳትፈዋል። ለዚህም 993 የፈተና ጣቢያዎችና 16 ሺህ 36 የሰው ኃይል ተደራጅቶ ሲንቀሳቀስ እንደነበርም ተመልክቷል። የፈተናውን መጠናቀቅ አስመልክቶ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መሃመድ አህመድ በሰጡት መግለጫ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲሰጥ የነበረው የአስረኛና የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ፈተና በሰላም ተጠናቀዋል ብለዋል። ለዚህም ተፈታኝ ተማሪዎች፣ ወላጆች፣ መምህራን፣ ሚዲያዎች፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና የፀጥታ ኃይሎች ያበረከቱት አስተዋጽኦ የጎላ እንደነበር ገልፀዋል። ይሁን እንጂ በፈተናው ወቅት ያልተፈቀዱ ቁሳቁሶችን ይዞ መግባትና ለሌሎች ተፈታኞች ፈተናውን የመውሰድ ሙከራዎች ተስተውለው ነበር ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በዚህ ተግባር በተገኙት ላይም ህጋዊ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል። በሀገሪቷ አሁን የተፈጠረው ሰላምና መረጋጋት ተማሪዎች በተረጋጋ መንገድ ፈተናቸውን እንዲሰሩ ያስቻላቸው ከመሆኑም በላይ የፈተና መርሃ ግብሩም  በስኬት አንዲጠናቀቅ አስችሏል ተብሏል። ፈተናው በሰላማዊ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ሚናቸውን ሲጫወቱ ለነበሩ ሁሉ ሚኒስቴሩ ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም