ያለ ህብረተሰብ ፍላጎት የተቆፈረ የጋራ መጸዳጃ ጉድጓድ የጤናና ማህበራዊ እክል እያስከተለ ነው-ነዋሪዎች

94
አዲስ አበባ ግንቦት 30/2010 በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 በተለምዶ ግንፍሌ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ያለ ህብረተሰብ ፍላጎት በወረዳው አነሳሽነት ለመጸዳጃ ቤት የተቆፈረ ጉድጓድ ለከፍተኛ የጤና ችግርና ማህበራዊ ቀውስ ዳርጎናል ሲሉ ነዋሪዎች ገለጹ። የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 አስተዳደር በበኩሉ መጸዳጃ ቤቱ እንዲሰራ የተፈለገው በአካባቢው ማህበረሰብ ጥያቄ መሆኑንና ቦታ ከማመቻቸት ያለፈ ኃላፊነት እንደሌለበት አስታውቋል። ችግሩ የሚመለከተው የግንባታው ባለቤት የሆነውን የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የጉለሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ነው በማለትም ተጠያቂ አድርጓል። የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የጉለሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በበኩሉ የመጸዳጃ ቤት ግንባታው "የአካባቢውን ህብረተሰብ  ለከፍተኛ የጤና ችግርና ማህበራዊ ቀውስ የሚዳርግ በመሆኑ ጉድጓዱ እንዲደፈን ለወረዳው ትዕዛዝ አስተላልፌያለሁ" ብሏል። ኢዜአ ያነጋገራቸው የግንፍሌ አካባቢ ነዋሪዎች ያለ ህብረተሰቡ ጥያቄና ፍላጎት  ለመጸዳጃ ቤት በተቆፈረ ጉድጓድ ለከፍተኛ የጤና ችግር መዳረጋቸውን ገልጸው፤ ውሃ ያቆረው ጉድጓድ ደግሞ ለህፃናትና ለአዋቂዎችም የስጋት ምንጭና ለማህበራዊ ቀውስ እንደዳረጋቸው ነው የገለፁት። በተጨማሪም ነዋሪዎቹ ህብረተሰቡ የመፀዳጃ ቤቱን መገንባት እንደማይፈልግ በፊርማ አሰባስበው ጥያቄያቸውን ለወረዳው ኃላፊዎች ባቀረቡበት ወቅት "የልማት አደናቃፊ ናችሁ" የሚል ምላሽ እንደሚሰጧቸው በመግለፅ ወረዳው አስተዳደራዊ በደል እያደረሰባቸው መሆኑን ተናግረዋል። የአራዳ ክፍለ ከተማ ምግብ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ነሃሴ 29 ቀን 2009 ዓ.ም ለወረዳ 6 አስተዳደር የሚገነባው መጸዳጃ ቤት ለጤና ስጋት በማይሆን መልኩ ከመኖሪያ ቤቶቹ ቢያንስ 50 ሜትር ርቆ እንዲሰራ አስተያየት ቢሰጥም የተቆፈረው ጉድጓድ ግን ከመኖሪያ ቤቶቹ 2 ሜትር እንኳን ርቀት የለውም። የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 አሰተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉብርሃን ወልደስላሴ፤ በአካባቢው ህብረተሰብ ዘንድ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ "የመጸዳጃ ቤት ይሰራልን" ጥያቄ መኖሩን ገልፀዋል። አቶ ሙሉብርሃን፤ የጋራ መጸዳጃ ቤቱ ግንባታ የአብዛኛው አባወራ ጥያቄ መሆኑን አስረድተው፤ "መፀዳጃ ቤቱ እንዲሰራ የማይፈልጉ ጥቂት ሰዎች ይኖራሉ ነገር ግን በግዳጅ የተሰራ ነገር የለም" ብለዋል። የመፀዳጃ ቤቱ ግንባታ የአብዛኛው ህብረተሰብ ጥያቄ ከሆነ ለምን ተቆፍሮ ለረጅም ጊዜ ሳይሰራ ሊቆይ ቻለ? ለሚለው ጥያቄ አቶ ሙሉብርሃን በሰጡት ምላሽ ወረዳው ቦታ ከማመቻቸት ያለፈ ሥራ እንደሌለውና ችግሩ የግንባታው ባለቤት የሆነው የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የጉለሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። የሚገነባው መጸዳጃ ቤት ለህብረተሰቡ የጤና ስጋት በማይሆን መልኩ ከመኖሪያ ቤቶቹ ቢያንስ 50 ሜትር ርቆ ለምን እንዲሰራ ማድረግ አልተቻለም? ለሚለው ጥያቄ፤ በወረዳው የማህረሰብ አቀፍ ልማት ኃላፊ አቶ አብነት ዳኜ በሰጡት ምላሽ  "ያው ከጤና ጋር ተያይዞ ከእስታንዳርድ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ነባራዊ ሁኔታ ከባድ ነው።50 ሜትር ርቆ መፀዳጃ ቤት መስራት ይከብዳል" ብለዋል የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የጉለሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፍሳሽ መስመር  የጋራ መኖሪያ ቤቶች ጥናትና ዝርጋታ ፣ ማዘዋወር ንዑስ የስራ ሂደት መሪ ወይዘሮ ትዝታ ወልዴ በበኩላቸው፤ የመጸዳጃ ቤት ግንባታው የአካባቢውን ህብረተሰብ  ለከፍተኛ የጤና ችግርና ማህበራዊ ቀውስ የሚዳርግ በመሆኑ ጉድጓዱ እንዲደፈን ለወረዳው ትዕዛዝ መተላለፉን ተናግረዋል። የምግብ፣የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 661/2009 ስለግንባታ ሥራዎች በሚመለከተው አንቀፅ 25 ለማንኛውም አገልግሎት የሚውል ግንባታ የሚያካሄድ ማንኛውም ሰው፤ አስፈጻሚ አካሉ ከሕዝብ ጤና አጠባበቅ አንጻር የሚያወጣቸውን መስፈርቶች ማክበር እንዳለበት ይደነግጋል። የልማት ፖሊሲና ስትራቴጂዎች የህብረተሰቡን ጥያቄና ፍላጎት ባገናዘበ መልኩ ሊተገበሩ እንደሚገባ ቢገለጽም ይህ ከህብረተሰቡ ፍላጎት ውጭ የተቆፈረው የጋራ መጸዳጃ ጉድጓድ እያደረሰ ያለው የጤናና ማህበራዊ  ችግር ህዝብን ያለማድመጥ ችግርን አመላካች ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ ህዝቡን በማማረር በመንግስት ላይ የከረረ ተቃውሞና ቅሬታ እንዲኖር የሚያደርግ አመራር እንዲሁም በአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ላይ ድክመት ያሳየና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የማይፈታ አመራር "ተግባሩ የማይታለፍና ቀይ መስመር ውስጥ ያለ ነው" ሲሉ አጽንኦት መስጠታቸው የሚታወስ ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም