ግጭቶችና አለመግባባቶችን በእርቅና ይቅርታ መፍታት ይገባል- የቤንች ሸኮ ዞን የአገር ሽማግሌዎች

73

ሚዛን ግንቦት 25 / 2011 ግጭቶችና አለመግባባቶችን በእርቅና ይቅርታ መፍታት እንደሚገባ የቤንች ሸኮ ዞን የአገር ሽማግሌዎች ገለጹ፡፡

የአገር ሽማግሌዎቹ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ግጭቶችና አለመግባባት የተፈጠረባቸው ወገኖች ችግራቸውን በመነጋገር መፍታት አለባቸው።

አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል ቄስ ተስፋዬ ገብረ መድህን እንዳሉት ግጭቶችን በይቅርታ መፍታት በሁለቱም ወገኖች መተማመንን ይፈጥራል፡፡

ቄስ ተስፋዬ ግጭቶች በዘላቂነት የሚፈቱት የተጋጩ ወገኖች ልዩነታቸውን በዕርቅና ይቅርታ ሲፈቱ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

መንግሥትም የሚከሰቱ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን በባህላዊ እርቅ የመፍታት ባህልን ማበረታታት እንዳለበትም ቄስ ተስፋዬ አመልክተዋል፡፡

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ አቤል ዶርቴት በበኩላቸው በይቅርታ የሚያምንና ይቅር ባይ ትውልድ ማፍራት እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡

በቅርቡ በሸኮና ቤንች አካባቢ የነበረው ግጭት በእርቅ መፍትሔ ማግኘቱን እንደ አብነት የጠቀሱት የአገር ሽማግሌ፣ልምዱ ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡ ለባህላዊ ህግጋቶች ያለው አመለካከት የዳበረ በመሆኑ መንገድ ግጭቶችን በባህላዊ መንገድ መፍታት ዋስትና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ለወጣቱ ትውልድ አገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎችን ማስተማር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ግጭቶችንና አለመግባባቶችን በእርቅና ይቅርታ መፍትሔ እንዲያገኙ የጀመረው እንቅስቃሴ የሚበረታታ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ አቶ ብርሐኑ ዘውዴ የተባሉ አገር ሽማግሌ ናቸው፡፡

''አገር በቀል አስተምህሮቶችን ማስረጽና መጠቀም ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላል''ሲሉም ተናግረዋል።

መንግሥትም የግጭት መንስዔዎች ላይ አተኩሮ እንዲሰራ ጠይቀዋል።

 የሁሉም ነገር መሰረት የሆነውን ሰላም ለማስፈን ሕዝቡና መንግሥት ተቀናጅተው መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም