በሆሮ ጉዱሩ፣ ቄለም ወለጋና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች ለፈተና ዝግጅት ተደርጓል

71

ግንቦት 24/2011 በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ፣ ቄለም ወለጋና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች በመጪው ሰኔ ወር የሚሰጡ ሀገር አቀፍና ክልላዊ ፈተናዎች ያለምንም ችግር እንዲጠናቀቁ ዝግጅት መደረጉን የየዞኖቹ ትምህርት ጽህፈት ቤቶች አስታወቁ።

የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የትምህርት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ደጀኔ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ በሁሉም ወረዳዎች የ8ኛ፣ የ10ኛ እና የ12ኛ ክፍል ፈተናዎች ይሰጣሉ።

ፈተናው ያለምንም የጸጥታ ችግር የፈተና ሕግና ደንብን ተከትሎ እንዲሰጥና ኩረጃን ለመከላከል ከዞን ጀምሮ እስከ ትምህርት ቤት ድረስ የታክስ ፎርስ ኮሚቴ ተዋቅሮ የራሱን ዕቅድ በማዘጋጀት ወደሥራ መግባቱን ገልጸዋል ፡፡

በአሁኑ ወቅት በዞኑ ለብሔራዊ ፈተና ለሚቀመጡ 39 ሺህ767 ተማሪዎች 414 ፈታኞች፣ 128 ሱፐርቫይዘሮች እና 46 የፈተና ጣቢያ ኃላፊዎች ምደባ ተጠናቅቆ ለወረዳዎች መተላለፉንም አስረድተዋል፡፡

በዘንድሮ ዓመት ፈታኞችና ተቆጣጣሪዎች ከዞኑ የተመደቡ ቢሆንም ከወረዳ ወረዳ እንዲቀያየሩ መደረጉን የገለጹት አቶ ደጀኔ  የፈተና ጣቢያ ኃላፊዎችም ከምስራቅ ወለጋ፣ ከነቀምቴ ከተማ አስተዳደርና ከምዕራብ ሸዋ መመደባቸውን ተናግረዋል ፡፡

በተመሳሳይ የቄለም ወለጋ ዞን 40 ሺህ 81 ተማሪዎችን ለማስፈተን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን የዞኑ የትምህርት ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ኬኔሣ ቀልቤሳ እንዳታወቁት በዞኑ በሚገኙ366 የፈተና መስጫ ጣቢያዎች ብሔራዊ ፈተናዎቹ ያለ ጸጥታ ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲሰጡ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል።

ለእዚህም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆንና በየደረጃው ታክስ ፎርስ በማደራጀት በዕቅድ ወደሥራ መገባቱን ነው የገለጹት ፡፡

የጸጥታ ችግር ባለባቸው በሰዮ፣ አንፊሎ፣ ግዳሚ፣ የማሎጊ ወለል፣ ጅማ ሆሮ እና ጋዎ ቄቤ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ 10 ትምህርት ቤቶች ፈተናው በሰላማዊ መንገድ እንዲሰጥ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ መወሰኑንም ገልጸዋል፡፡

የሻምቡ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት ቸሪነት ጀማል በበኩላቸው ተማሪዎች ለፈተና በሚቀመጡበት ጊዜ የፈተናውን ሕግና ደንብ ተከትለው በራሳቸው ፈተናውን መስራት እንዲችሉ ግንዛቤ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

“ኩረጃ አጸያፊ ተግባር በመሆኑ ራሳቸውን ከእዚህ ተግባር ማራቅ እንዳለባቸው ከተማሪዎች ጋር ውይይት ተደርጓል” ብለዋል።

በተያያዘ ዜና በምዕራብ ሸዋ ዞን ዘንድሮ የሚሰጡትን አገራዊና ክልላዊ ፈተናዎች ከኩረጃ የጸዱ ለማድረግ የዝግጅት ሥራ እየተጠናቀቀ መሆኑ ተገልጿል።

“ሌብነትን አስወግደን የፈተና ስርአት በማዘመን ጥራት ያለው የፈተና ሂደት እናስፍን” በሚል መሪ ቃል የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት በአምቦ ከተማ ከባለድርሻ አካላትን ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ዶክተር ፈቀደ ቱሊ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የፈተና አሰጣጡ በተቃና ሁኔታ እንዲካሄድ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

 “የምክክሩ ዓላማም ባለፈው ዓመት ድክመቶች ላይ ተመስርተን ዘንድሮ ድክመቶቹን በምን መልኩ ማስወገድ እንደሚገባ ለመመካከር ነው” ብለዋል፡፡

በውይይቱ የፈተና ስርአቱ የተሳካና ስነመግባር የተሞላበት እንዲሆን የጋራ አቅጣጫ እንደሚያዝም አመለክተዋል፡፡

ዶክተር ፈቀደ እንዳሉት በየትምህርት ቤቶች የፈተና አፈጻጸምን የሚከታተል ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ተሰጥቷል፡፡

“ኮማንድ ፖስቱ የፈተና ወረቀቶቹ ከሚጓጓዙበት ጊዜ ጀምሮ ፈተናው እስከሚጠናቀቅ ደህንነቱ ተጠብቆ እንዲቆይና በፈተና ስፍራዎች ችግር እንዳይፈጠር የቅርብ ክትትል ያደርጋል” ብለዋል፡፡

ሌብነትን የሚጸየፍ ተማሪን ለመፍጠርና የፈተና ስርቆትን ለማስቀረት ከወላጆች፣ አባገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ መምህራንና ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑንም ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ የወረዳ አስተዳዳሪዎች ፣ የትምህርት ባለሙያዎች፣ የትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች፣ ዳይሬክተሮች፣ የፈተና ክፍል ኃላፊዎች ፣የፀጥታና የፍትህ አካላት፣ አባገዳዎች የሀገር ሽማግሌዎች መሳተፋቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም